በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ምክንያት በመዲናዋ ለተሽከርካሪ ዝግ የሚሆኑ መንገዶች ይፋ ሆኑ

97

አዲስ አበባ፣  ጥር 25/2014 (ኢዜአ)  በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ምክንያት በመዲናዋ ለተሽከርካሪ ዝግ የሚሆኑና ተሽከርካሪ ማቆም የተከለከለባቸው መንገዶች ይፋ ሆነዋል፡፡

ለጉባኤው ዝግጅት የተቋቋመውን የጸጥታና ደህንነት ግብረ ኃይል መግለጫ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ከአዋሬ በጥይት ቤት ወደ ፓርላማ እንዲሁም ከቡልጋሪያ ወደ አፍሪካ ህብረት የሚወስዱ መንገዶች በሁለቱም አቅጣጫ የስብሰባው ተካፋዮች ጠዋት ለስብሰባ ፣ ለምሳና ከሰዓት በኋላ ከስብሰባ ሲወጡ ለተሽከርካሪ ዝግ ይሆናሉ።

ግብረ ኃይሉ በተጨማሪ ከዓርብ ጥር 27 ቀን 2014 ዓ. ም ጀምሮ ጉባኤው እስኪጠናቀቅ በሁለቱም አቅጣጫ ተሽከርካሪ ማቆም የተከለከለባቸውን መንገዶች ይፋ አድርጓል፡፡

በዚህም  ከፓርላማ መብራት፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፡  መስቀል አደባባይ፣   ፍላሚንጎ፣   ኦሎምፒያ፣  ወሎ ሰፈር፣ ጃፓን ኤምባሲ፣ ፍሬንድ ሺፕ፣ ቦሌ ቀለበት መንገድ፣ ኤርፖርት እንዲሁም:-

ከፓርላማ መብራት፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በብሔራዊ ቤተ-መንግስት፣ በፍልውሃ፣  በብሔራዊ ቲያትር፣ ሜክሲኮ አደባባይ፣ አፍሪካ ህብረት አዳራሽ ዙሪያ ከተጠቀሰው ጊዜ ጀምሮ ተሽከርካሪዎችን ማቆም እንደማይቻል ግብረ ኃይሉ አስታውቋል፡፡

በተመሳሳይ ከፓርላማ መብራት፣ብሔራዊ ቤተ-መንግስት፣ ወዳጅነት ፓርክ፣ ንግድ ማተሚያ ቤት፣  ሞናርክ ሆቴል፣ ቴዎድሮስ አደባባይ፣ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል፣ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ ብሔራዊ ቴአትር፣  ሜክሲኮ አደባባይ፣ አፍሪካ ህብረት እንዲሁም ከፓርላማ መብራት፣ በሸራተን ሆቴል ቁልቁለቱን፣ፍልውሃ እና አምባሳደር ቲአትር ዙሪያውን ተሽከርካሪ ማቆም እንደማይቻል ገልጿል።

በተጨማሪ ከንግድ ምክር ቤት ጀምሮ በሱዳን ኤምባሲ፣ አፍሪካ ህብረት ዋናው በር ሳርቤት ድረስ በሁለቱም አቅጣጫዎች ግራና ቀኝ ለአጭርም ሆነ ለረጅም ጊዜ ተሽከርካሪ አቁሞ መሄድ ፍጽሞ የተከለከለ ነው ብሏል ግብረ ኃይሉ፡፡

በመሆኑም ከጦር ሃይሎች ወደ ሜክሲኮ አደባባይ ለሚመጡ አሽከርካሪዎች በኮካ-ኮላ ድልድይ፣ በአብነት ተክለ ኃይማኖት ወይም በሞላ ማሩ፣ ጌጃ ሰፈር ጎማ ቁጠባ ተለዋጭ መንገድ መጠቀም እንደሚችሉም አስታውቋል።

ከሳር ቤት ወደ ሜክሲኮ የሚመጡ አሽከርካሪዎች ደግሞ ሳር ቤት ካርል አደባባይ በልደታ አድርገው ወደ መርካቶ እና ጎማ ቁጠባ መጓዝ ይችላሉ ተብሏል፡፡

የቦሌ መንገድ ተጠቃሚዎች በአትላስ፣  ዘሪሁን ህንፃ፣ ሲግናል፣ቀለበት መንገድ፣ ቦሌ ሚካኤል፣ ሃኪም ማሞ፣  ወደ ጎተራ ፣ ቀለበት መንገድ፣ መገናኛ ዲያስፖራ አደባባይ፣  እንግሊዝ ኤምባሲ፣ ቀለበት መንገድ መገናኛ፣   አድዋ ጎዳና፣   አዋሬ፣ ቤልኤር፣ በፍላሚንጎ ደንበል ጀርባ መስቀል ፍላወር  መጠቀም እንደሚቻልም የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታውቋል፡፡

እንግዶቹ ለልዩ ልዩ ጉዳይ በአጀብ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ለእንግዶች ቅድሚያ በመስጠት፣ ለአጀብ ስራ መንገድ ሲዘጋ ለተሽከርካሪ ክፍት እስከሚሆን ድረስ አሽከርካሪዎች  ትዕግስት ተላብሰው በመጠበቅ አስፈላጊውን  ትብብር እንዲያደርጉ  የጋራ ግብረ-ኃይል ጥሪ አቅርቧል።

ጉባኤው ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲጠናቀቅ ኀብረተሰቡ ከጸጥታ አካላት ጎን በመቆም የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንዲያደርግም ግብረ-ኃይሉ ጠይቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም