በዞኑ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ 119 ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ማስወገድ ተችሏል- መምሪያው

190

ጂንካ፤ ጥር 22/2014 (ኢዜአ)፡ በደቡብ ኦሞ ዞን ቆላማ አካባቢዎች በሴቶች ላይ ከሚፈጸሙ 140 ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ውስጥ 119ኙን ማስወገድ መቻሉን የደቡብ ኦሞ ዞን ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ መምሪያ አስታወቀ።

በሴቶች የልማትና የለውጥ ፓኬጅ አተገባበርና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አወጋገድ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በደቡብ ኦሞ ዞን በና-ፀማይ ወረዳ ቀይ- አፈር ከተማ ትላንት ተካሂዷል ።

የደቡብ ኦሞ ዞን ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ምህረት በላይ በምክክር መድረኩ ላይ እንደገለጹት በዞኑ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቀረት ህብረተሰቡን፣ የሃይማኖት አባቶችንና የሀገር ሽማግሌዎችን ያሳተፈ የንቅናቄ ስራ ተሰርቷል።

በተሰሩ ስራዎች በዞኑ  በሴቶች ላይ ይፈጸማሉ ተብለው ከተለዩ 140 ዋና ዋና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች 119 የሚሆኑትን ሙሉ ለሙሉ ማስወገድ መቻሉን አመላክተዋል።

ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ከማስወገድ ባሻገር የሴቶች ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በልማት ቡድኖች በማደራጀት ተጠቃሚ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

 በትብብር የተሰራው ስራ በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ላይ ውጤት እንዲያስገኝ ማስቻሉን የገለጹት ደግሞ የደቡብ ኦሞ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደሞ በዛብህ ናቸው።

''የሴቶች ጉዳይ ለሴቶች መዋቅር ብቻ የሚተው አይደለም'' ያሉት አቶ ደሞ፤ በተለይ የሴቶችን ዘላቂ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ባለድርሻ አካላት የሴቶችን ጉዳይ እንደ አንድ የስራ አካልና ቀዳሚ አጀንዳ አድርጎ መውሰድና መፈጸም እንደሚገባ አመልክተዋል።

የደቡብ ኦሞ ዞን ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ መምሪያ  የሴቶች ንቅናቄና ተሳትፎ ማስፋፊያ ቡድን መሪ ወይዘሮ ውብሸት መኮንን በበኩላቸው በዞኑ  በተለይ ሴቶችን መሰረት አድርገው ከሚፈፀሙ 140 ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች  119 የሚሆኑትን ማስወገድ ተችሏል ።

ቀሪዎቹ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች የሴቶችን የትምህርት ተሳትፎ ወደ ሁዋላ ያስቀሩና በፍጥነት ሊወገዱ የሚገባቸው መሆኑን ጠቁመዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ወሊ ኃይሌ በሰጡት አስተያየት፤የሴቶችን የትምህርት ተሳትፎ ለማሳደግና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትታቸውን ለማረጋገጥ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ የደቡብ ኦሞ ዞን ፍትህ መምሪያ ኃላፊ አቶ ተመስገን ጋርሾ ፤በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን ለመከላከል የፍትህ ተቋማት ተቀናጅተው እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በዘርፉ መልካም ውጤት መገኘቱን የጠቀሱት አቶ ተመስገን፤ በተለይም ለሴቶች ተጠቃሚነት ተግዳሮት ሆነው የቀጠሉ ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስወገድ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በሴቶች የልማትና የለውጥ ፓኬጅ አተገባበር ዙሪያ በተዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ የሴቶች የጤናና የስነ-ተዋልዶ ስርዓትን ማጎልበት፣የሴቶችን የትምህርት ተሳትፎ ማሳደግ፣የመሬት ባለቤትነት ማረጋገጥ ፣የውሳኔ ሰጭነት ድርሻቸውን ማሳደግ የሚሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተካሂዷል።

በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃትን መመከትና  ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን መከላከልና ማስቆም በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ  የተለያዩ ጥናታዊ ፁሑፎች ቀርበው ምክክር ተደርጓባቸዋል።

በቀረበው ጥናታዊ ፁሑፍም በዞኑ በተለይ አርብቶ አደር አከባቢዎች ሴትን የሀብት ምንጭ አድርጎ የመመልከት፣ያለ እድሜዋ መዳርና ሴቶችን ወደ ትምህርት ቤት አለመላክ የመሳሰሉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች የሴቶችን የትምህርት ተሳትፎ አነስተኛ እንዲሆን ማድረጉ ተጠቁሟል።

በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ሙሉ በሙሉ ለመመከት የሴቶች የልማት ቡድን አደረጃጀቶችን ማጠናከርና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባም ተገልጿል።

የምክክር መድረኩን የደቡብ ኦሞ ዞን ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ መምሪያ ከጅንካ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት መሆኑ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም