በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ ከተሞችን መልሶ ለመገንባት የሁሉም ድጋፍና ርብርብ ያስፈልጋል

64

አዲስ አበባ ፣ ጥር 24/2014(ኢዜአ) በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ ከተሞችን መልሶ ለመገንባትና የተሟላ አገልግሎት ለማስጀመር ሁሉም ዜጋ ድጋፍና ርብርብ እንዲያደርግ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ ጥሪ አቀረቡ፡፡

አሸባሪው ህወሓት በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች ያወደማቸውን ከተሞች መልሶ መገንባት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ የሚመክር መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሔደ ነው።

በተለይም ዳያስፖራዎች በከተሞች ግንባታና በቤቶች ልማት ፕሮግራሞች ላይ መሳተፍ በሚችሉበት ሁኔታም ላይ ይነጋገራሉ።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ፤ በውይይት መድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ ከተሞችን መልሶ ለመገንባትና የተሟላ አገልግሎት ለማስጀመር የሁሉም ዜጋ ድጋፍና ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል።

አሸባሪ ቡድኑ በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች ከፍተኛ የኢ-ሰብአዊ ድርጊት ፈፅሟል፣ ከተሞችን አውድሟል፣ ዘርፏል፣ መሰረተ ልማቶች ላይ በማተኮርም ውድመት ፈፅሟል።

በመሆኑም ጉዳት የደረሰባቸውን ከተሞች መልሶ የመገንባት ስራ መጀመሩን የጠቀሱት ሚኒስትሯ የታቀደውን ለማሳካት የሁሉም ድጋፍ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በየትኛውም ዓለም የሚገኙ ዳያስፖራዎች፣ ባለሃብቶች፣ ባለሙያዎች እና አጠቃላይ ህዝቡ ለመልሶ ግንባታ የሚችለውን ሁሉ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የወደሙ ከተሞችን ማዘጋጃቤታዊ ስራዎች መልሶ ለማስጀመር፣ መሠረተ ልማቶችን በፍጥነት ገንብቶ የተሟላ አገልግሎት ለማስጀመር በጋራ መስራት አለብን ብለዋል።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን በጋራ ባዘጋጁት የምክክር መድረክ ሚኒስትሮች፣ የዳያስፖራ ኤጀንሲ ሃላፊዎች፣ ዳያስፖራዎችና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት  ተወካዮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም