በክልሉ የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ መልቀቂያ ፈተና ላልወሰዱ ተማሪዎች እየተሰጠ ነው

238

ባህርዳር ፣ ጥር 24/2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል በፀጥታ ችግር ምክንያት ቀደም ሲል የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ መልቀቂያ ፈተና ያልወሰዱ ከ37 ሺህ በላይ ተማሪዎች ዛሬ መሰጠት መጀመሩን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የፈተና ዝግጅትና አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ ኃይሉ ታምር ለኢዜአ እንደገለጹት ፈተናው በየአካባቢው በተቋቋሙ 129 የፈተና ጣቢያዎች ዛሬ መስጠት ተጀምሯል ።

ፈተናው የ12ኛ ብሄራዊ መልቀቂያ ፈተና ለተከታታይ አራት ቀናት የሚሰጥ ሲሆን፤ ከ1 ሺህ 330 የሚበልጡ መምህራን፣ ሱፐርቫይዘሮችና ተቆጣጣሪዎች መሰማራታቸውንም ተናግረዋል።

ፈተናው እየተሰጠ ያለው በክልሉ አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት ምክንያት ቀደም ሲል የተሰጠው ፈተና ባልተሰጠባቸው ደቡብና ሰሜን ወሎ፣ ዋግኸምራ፣ ኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞኖችና በደሴ ከተማ አስተዳደር መሆኑን አብራርተዋል።

በተጨማሪም በክልሉ የሰሜን ሸዋ ዞን ሶስት ወረዳዎች፣ በሰሜን ጎንደር ዞን በአንድ የፈተና ጣቢያ ፈተናው በሰላም መሰጠት መጀመሩን  ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች ተፈናቅለው ለመጡ 220 ተማሪዎችም በልዩ ሁኔታ በቡሬ ከተማ በተቋቋመ የመፈተኛ ጣቢያ እየተፈተኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በአጠቃላይ ብሄራዊ መልቀቂያ ፈተናውን እየወስዱ ካሉ ተማሪዎች መካከል 73ቱ አይነስውራን መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

ለፈተናው የሚያስፈልጉ ቁሳቁስና የፈተና ወረቀቶች ቀደም ሲል በሁሉም የፈተና ጣቢያዎች ተሟልተው መድረሳቸውን አስረድተዋል።

ቡድን መሪው እንዳሉት  ፈተናው ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው የፀጥታ ስምሪት ተደርጓል።

ባለፈው ጥቅምት ወር መጨረሻ በተሰጠው ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ መልቀቂያ ፈተና ሰላማዊ በሆኑ የክልሉ አካባቢዎች 124 ሺህ 920 ተማሪዎች ፈተናውን መውሰዳቸው ይታወቃል።