የባህል፣ ዕደ ጥበብና ኪነ ጥበብ ዘርፍ ለልማት ያለውን ሚና ለማሳደግ እየተሰራ ነው

446

አዳማ፣ ጥር 23/2014( ኢዜአ) የባህል፣ ዕደ ጥበብና ኪነ ጥበብ ዘርፍ በሀገሪቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ያለውን ሚና ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ አስታወቁ።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ግምገማውን በአዳማ ከዘርፉ መሥሪያ ቤቶች ጋር ገምግሟል።

ሚኒስትሩ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፉት ዓመታት የባህል፣ የዕደ ጥበብና ኪነ ጥበብ ዘርፍ በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት ውስጥ የሚጫወተውን ሚና ከፍ ለማድረግ እየተሰራ ነው።

''የባህል እሴቶች፣ ዕደ ጥበብና ኪነ ጥበብ በሀገር ገፅታ ግንባታ ጉልህ ሚና ሊኖራቸው ይገባል'' ያሉት አቶ ቀጄላ፣ ይህን የሚሆነው ተገቢውን ትኩረት አግኝተው መልማትና መዘመን ሲችሉ መሆኑን አስረድተዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት የባህል እሴቶች በህዝቦች መቻቻልና አብሮነት በተለይ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር መሰራቱን አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ ብሔራዊ የስፖርት መሠረተ ልማት ግንባታን ለማፋጠን ጥረት መደረጉን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

በሚኒስቴሩ የባህልና ቋንቋ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ወርቅነሽ ብሩ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከገጠሟት ችግሮች ለመውጣት የባህል እሴቶች ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።

ባህላዊ የግጭት አፈታትና እርቅ ሥርዓትና ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ልዩነታችን ውበታችን ከመሆን ባለፈ የአንድነት ምልክት በመሆናቸው ዘርፉን ለማልማት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዚህም በሕዝቦች መካከል ጠንካራ የባህል ትስስርና ግንኙነት በመፍጠር ትኩረት መሰጠቱን ሚኒስትር ዴኤታዋ አስረድተዋል።

ባህላዊ እሴቶች የችግሮች መፍቻ እንዲሆኑ የተቀናጀ ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።

በቋንቋ ልማት በኩል ስድስት ጥናቶች ተካሄደዋል ያሉት ወይዘሮ ወርቅነሽ፣ በዚህም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቋንቋዎችን ያሉበትን ሁኔታ በመለየት በሰነድ አደራጅቶ ለመያዝ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከአማርኛ በተጨማሪ አፋን ኦሮሞ፣ ሶማሊኛ፣ አፋርኛና ትግሪኛን የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ ለማድረግ ረቅቅ የፖሊሲ ሰነድ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ዘርፉ በሀገሪቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትና ዕድገት ሚናውን እንዲወጣ የተጠናከረ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን በሚኒስቴሩ የዕደ ጥበብና ኪነ ጥበብ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ነፊሳ አልማዲ ተናግረዋል።

የኪነ ጥበብ ማህበራትን ባሳተፈ መልኩ የዘርፉን ፖሊሲ ከመፈተሽና ስትራቴጂዎችን ከመቅረፅ ጀምሮ የአሰራርና አደረጃጀት ችግሮችን ጭምር ለመፍታት ያስችላል ብለዋል።

ኪነ ጥበብና ዕደ ጥበብ ህዝብ ለህዝብ ትስስርና አንድነት የጎላ ሚና ያላቸው በመሆኑ ''ድንቅነሽ'' በሚል ስያሜ ፕሮጀክት ተቀርፆ በክልሎች የኪነ ጥበብ ሥራዎችን ለሕዝብ ለማቅረብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የሐረር የስፌት ዓይነቶችና የጋምቤላ የእደ ጥበብ ሥራዎችን በኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽህፈት አስመዝግቦ የባለቤትነት መብት እንዲያገኙ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ወይዘሮ ነፊሳ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም