ለዘላቂ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የሴቶች አመራርነት ተሳትፎ ወሳኝ ነው

167

አዲስ አበባ፣ ጥር 24/2014 (ኢዜአ)  ለዘላቂ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የሴቶች አመራርነት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ፡፡

በፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አነሳሽነት በመካከለኛ የአመራር ደረጃ የሚገኙ ተተኪ ሴት አመራሮችን ለማፍራት የተዘጋጀ የአቅም ግንባታ ስልጠና በአፍሪካ የአመራር ልህቀት አካዳሚ እየተሰጠ ነው፡፡

ስልጠናው በመካከለኛ አመራርነት ያሉ ሴቶችን በመሪነት ክህሎት በማብቃት ወደ ከፍተኛ አመራርነት ለማምጣት ያለመ ነው ተብሏል።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ የተጀመረው የለውጥ ጉዞ በሁሉም መስክ ሴቶችን ተሳታፊ ማድረግ አለበት፡፡

ለዘላቂ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የሴቶች የአመራርነት ተሳትፎ ወሳኝ ሚና እንዳለውም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በዚህም በአገር አቀፍ ደረጃ በተነደፈው የ10 ዓመት መሪ የልማት እቅድ ላይ የሴቶችን የአመራርነት ተሳትፎ 50 በመቶ የማድረስ ግብ ተቀምጧል ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ ድህነትን ጨምሮ በማህበረሰቡ ዘንድ ያሉ ችግሮችን የሚቀርፉ አመራሮች ያስፈልጓታል ያሉት ፕሬዝዳንቷ፤ ከዚህ አኳያ ሴት አመራሮችን ማብቃት ተገቢ ነው ብለዋል፡፡

ስልጠናው በፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አነሳሽነት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግስታት የሴቶች ኤጀንሲ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው።

በስልጠናው ከሁሉም ክልሎች፣ ከመንግስትና የግል ተቋማት እንዲሁም ከሲቪል ማህበራት የተውጣጡ 60 በመካከለኛ አመራርነት ደረጃ ያሉ ሴቶች እየተሳተፉ ሲሆን፤ ስልጠናው ለ10 ቀናት የሚቆይ ይሆናል፡፡