የ14 አፍሪካ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አዲስ አበባ ገብተዋል

82

ጥር 24 ቀን 2014 (ኢዜአ) በ35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤና በ40ኛው የአስፈፃሚ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ለመካፈል 14 የአፍሪካ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ወደ አዲስ አበባ ገብተዋል።

እሁድ አመሻሽ ላይ የዚምባብዌ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ፍሬድሪክ ሻቫ እና የሳኦ ቶሜና ፕሪንሲፔ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤዲቴ ዶ ራሞስ ዳ ኮስታ ቴን-ዡዋ ማምሻውን አዲስ አበባ ገብተዋል።

ከትናንት ማምሻውን ብቻ እስከ ማለዳው 12 ሰዓት ድረስ የ12 አፍሪካ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በጉባኤው ለመሳተፍ ወደ አዲስ አበባ ገብተዋል።

የሶማሊያ፣ ካሜሩን፣ ቻድ፣ ኮትዲቯር፣ የሪፐብሊካዊት ኮንጎ፣ አንጎላ፣ ጅቡቲ፣ ሊቢያ፣ ሞሪታኒያ፣ ሴኔጋል፣ ደቡብ አፍሪካ እና ኒጀር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ናቸው ለጉባኤው አዲስ አበባ የገቡት።

በዚህ መሰረት የሶማሊያ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብዲሳድ ሙሴ አሊ፣ የቻዱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማህማት ዜኑ ሸሪፍ፣ የኮትዲቯር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካንዲያ ካሚስኮ ካማራ እና የካሜሮኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሌዡን ቤላ ቤላ ትናንት ምሽት አዲስ አበባ ገብተዋል።

የጂቡቲው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሙሀመድ አሊ የሱፍ ፣ የሊቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናጅላ አልማንጉሽ፣ የሪፐብሊካዊት ኮንጎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዢያን ክላውዴ እና የአንጎላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜንዶንካ ኤስሜራልዳም እኩለ ለሊት ላይ ቦሌ አለም ዓቀፍ አየር ማረፊያ ደርሰዋል።

በተመሳሳይ የሴኔጋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አይሳታ ታል ሳል ፣የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር እና የኒጀር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሀሱሚ ማሹዲ ማለዳውን አዲስ አበባ ገብተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም