የሆሞሻ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ምዕራፍ አስፋልት መንገድ ግንባታ ተጀመረ

72

አሶሳ፣  ጥር 23 / 2014 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሆሞሻ ህዳሴ ግድብ 100 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ መጀመሩን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

በባለስልጣኑ የምዕራብ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት አስተዳደር ቡድን አንድ መሪ አቶ ካሊድ ዓሊ ለኢዜአ እንደገለጹት የአስፋልት መንገዱ ግንባታ በሁለት ምዕራፎች ተከፍሎ የሚከናወን ነው።

የሆሞሻ  ህዳሴ ግድብ የአስፋልት መንገድ በአሶሳ በኩል ወደ አዲስ አበባ የሚያገናኘው ዋና መንገድ አካል መሆኑ ይታወቃል።

የአስፋልት መንገዱ የህዳሴው ግድብ ሲጠናቀቅ በአካባቢው የሚፈጠረውን ኢንቨስትመንት አማራጮች በማስፋት ለሀገሪቱ ምጣኔ ኃብታዊ ዕድገት አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተገልጿል።

መንገዱ የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ ከሆሞሻ ጀምሮ 70 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን መሆኑን ጠቁመው፤ በአሁኑ ወቅት የቅየሳ ስራው 80 በመቶ መጠናቀቁን ገልጸዋል።

ለዚሁ ለመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ የሚያገለግሉ የአሸዋና ድንጋይ መረጣና አቅርቦት ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

የመጀመሪያው ምዕራፍ የ70 ኪሎ ሜትሩ አስፋልት መንገድ ግንባታ በሶስት ዓመት ከስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ እንደሚከናወን ገልጸዋል።

መንገዱ በሚያቋርጣቸው የሆሞሻ፣ መንጌና ሸርቆሌ ከተሞች የ30 ሜትር  ከከተሞች ውጪ  ደግሞ 10 ሜትር ስፋት እንደሚኖረውም አስረድተዋል።

ለመንገድ ግንባታው የሚያስፈልገው ከ2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት በፌዴራል መንግሥት  እንደሚሸፈን ቡድን መሪው ጠቅሰዋል።

በሁለተኛው ምዕራፍ የሚገነባው እስከ ህዳሴ ግድብ ድረስ ያለውን ቀሪው 30 ኪሎ ሜትር መንገድ ግንባታ በተያዘው በጀት ዓመት ጨረታው እንደሚወጣ አቶ ካሊድ አስታውቀዋል።

የክልሉ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ የመንገድ ጥናት፣ ዲዛይንና ቁጥጥር ኮንትራት አስተዳደር ዳይሬክተር ኢንጅነር በፍቃዱ ዮሴፍ እንዳሉት ከግለሰቦች  ይዞታ ጋር ተያይዞ አለመግባባቶች እንዳይከሰቱ ከመንገድ ቅየሳ ጀምሮ በጋራ መሰራቱን አስረድተዋል።

ኢንጅነር በፍቃዱ እንዳሉት ይህም የመንገድ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ራሱን የቻለ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

የመንገዱ ግንባታ የጥራት ደረጃውን ጠብቆ እንዲካሄድ በቅንጅት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም  ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ከአሶሳ ወደ መተከል በሚወስደው መንገድ ላይ ለበርካታ ዓመታት በአሽከርካሪነት የሰሩት አቶ አዳነ እንድሪስ እንዳሉት በአካባቢው አገልግሎት እየሰጠ ያለው የጠጠር መንገድ ጉዞ ፈታኝ ነው።

የጠጠር መንገዱ ከህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር ተያይዞ ከባድ ተሸከርካሪዎች ምልልስ ስለሚበዛበት ቶሎ ቶሎ የሚበላሽ በመሆኑ ሌላው ለተሽከርካሪ ጉዞ አስቸጋሪ  መሆኑን ጠቁመዋል።

መንገድ ስራው ተጠናቆ ለአገልግሎት ሲበቃ ኅብረተሰቡ ፈጣን የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያደርግ በመሆኑ ለምጣኔ ኃብታዊ ዕድገት አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም