በጋምቤላ ክልልና በቡማ አስተዳደር ግዛት የጋራ ድንበር ሰላምና ልማትን ለማጠናከር ስምምነት ተፈረመ

119
ጋምቤላ ነሃሴ 24/2010 በኢትዮ-ደቡብ ሱዳን የድንበር ኮሚሽን በጋምቤላ ክልልና በደቡብ ሱዳን የቡማ አስተዳደር ግዛት የጋራ ድንበር ሰላምና ልማት ለማጠናከር የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈረመ ። በጋራ ድንበር ሰላምና ልማት ለማጠናከር በጋምቤላ ከተማ የተካሄደ የምክክር መድረክ ትናንት መጠናቀቁን ተከትሎ የመግባቢያ ሰነዱን የፈረሙት የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳር አቶ ጋትሉዋክ ቱትና የቡማ አስተዳደራዊ ግዛት ፕሬዘዳንት ደቪድ ያውያው ናቸው። የመግባቢያ ሰነዱ በምክክር መድረኩ የተላለፉ ውሳኔዎችና በጋራ ለመስራት የተደረሰባቸውን ስምምነቶች የያዘ ነው ። ስምምነት ከተደረሰባቸው ጉዳዮች መካከል ድንበር ዘለል ህፃናትን አፍነው የሚወስዱና የቀንድ ከብት ዘራፊዎችን እንቅስቃሴ ማስቆም፣ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያና የወርቅ ማዕድን ዝውውርን መግታት የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው ። በተጨማሪም የኮንትሮባንድ ንግድን መከላከል፣ ጸጥታ ማስከበር፣ የመረጃ ልውውጥ ማድረግ የሚሉት ተካተዋል ። ቀደም ሲል ታፈነው ተወስደው ያልተመለሱ ህፃናትና የተዘረፉ የቀንድ ከብቶች እንዲመለሱ፣ የሁለቱ የድንበር ተዋሳኞችን የህዝብ ለህዝብ፣ ምጣኔ ሀብታዊና የማህበራዊ ግንኙነቶች ማጠናከር የሚሉትም በምክክር መድረኩ የተላለፉ ውሳኔዎችና በሰነዱ የሰፈሩ ጉዳዮች ናቸው። የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጋትሉዋክ ቱት በወቅቱ እንደገለጹት ሰላም በሌለበት የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታዎችን ማፋጠን አይቻልም ። "የኢትዮጵያ መንግስት በአገር ውስጥ፣ በጉረቤትና በቀጠናው አገራት ሰላም እንዲሰፍን ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ ይገኛል" ብለዋል። በኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን የድንበር ኮሚሽን በጋምቤላ ክልልና በቡማ አስተዳደራዊ ግዛት የጋራ ስምምነት በድንበር አካባቢ ያልተፈቱ የሰላም እንቅፋቶችን ለመፍታት ፍሬያማ ውጤት እንደሚኖረው አመላክተዋል ። እንደ አቶ ጋትሉዋክ ገለፃ በመግባቢያ ሰነዱ የሰፈሩ ጉዳዮችን ወደ ተግባር ለመለወጥ የክልሉና የፌደራል መንግስት በትኩረት ይሰራሉ ። በደቡብ ሱዳን የቡማ አስተዳደር ግዛት ፕሬዝዳንት ዴቪድ ያውያው በበኩላቸው "የጋራ መግባቢያ ሰነዱ የሁለቱን የድንበር ተዋሳኝ ህዝቦች ግንኙነት ያጠናክራል " ብለዋል ። "የመግባቢያ ስምምነቱ በተለይም የሁለቱን የድንበር ተዋሳኝ ህዘቦች በጸጥታ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ጉዳዮች ተጠቃሚ ያደርጋል " ሲሉም ተናግረዋል። ፕሬዝዳንት ዴቪድ አክለውም የተደረሰው ስምምነት በድንበር ዘለል ችግር ፈጣሪዎች ታፍነው ተወስደው ያልተመለሱ ህፃናትና የተዘረፉ የቀንድ ከብቶችን ለመመለስ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ገልፀዋል። በመግባቢያ ሰነዱ በጋራ ለመስራት የተቀመጡትን የጸጥታ፣ የንግድ፣ የመንገድና ሌሎች ስምምነቶች በተሟላ ሁኔታ ለመፈጸም አስተዳደራቸው እንደሚሰራ ፕሬዘዳንት ዴቪድ አስታውቀዋል ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም