በኦሮሚያ ክልል ያለውን አንፃራዊ ሰላም ለማስቀጠል በጋራ እየተሰራ ነው

116
አዲስ አበባ  ነሀሴ 24/2010 በኦሮሚያ ክልል ያለውን አንፃራዊ ሰላም ለማስቀጠል የፀጥታ ኃይሉ ከህዝብ ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን የክልሉ የአስተዳደርና ፀጥታ ቢሮ  አስታወቀ። በክልሉ በቄሮ ስም ሕገ ወጥ ተግባራትን ሲያካሂዱ የነበሩ 600 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ገልጿል። የኦሮሚያ ክልል የአስተዳደርና ፀጥታ ቢሮ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ባይሳ ኩማ ለኢዜአ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት በክልሉ መረጋጋትና ሰላማዊ እንቅስቃሴ የሚታይ ሲሆን ይህን ለማስቀጠል የፀጥታ ኃይሉ ከህዝብ ጋር በጋራ እየሰራ ይገኛል። የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥና ለውጡን ለማስቀጠልም በየደረጃው ካሉ የኀብረተሰብ ክፍሎች ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል። በአንዳንድ ቦታዎች በቄሮ ስም የሚንቀሳቀሱ ሕገ ወጥ አካላት ለህግ የበላይነት እንዲገዙ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል። በክልሉ ለመጣው ለውጥ ወጣቶች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎች፣ ሴቶችና የምሁራን አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደ ነበርም አቶ ባይሳ አመልክተዋል። የክልሉ አስተዳደር ከሐይማኖት አባቶች፣ ከቄሮዎች፣ ከሴቶችና ከተለያዩ የኀብረተሰብ ክፍሎች ጋር በተካሄደ ውይይት አሁን የተገኘውን ለውጥና ሰላም ለማስቀጠል እንዲሁም የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የጋራ አቋም መያዙን አብራርተዋል። በኢትዮጵያ ለተጀመረው ለውጥ ቄሮ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ የገለጹት አቶ ባይሳ የፀጥታ ኃይሉ በቄሮ ስም ህገ ወጥ ተግባራት ሲያካሂዱ የነበሩ 600 ሰዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን ተናግረዋል። ዳይሬክተሩ እንዳሉት ከተለያዩ አደረጃጀቶች ጋር በተደረጉ ውይይቶች የብሔር ግጭት እንዲፈጠር እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ለህግ ለማቅረብ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል። በአሁኑ ወቅት የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል ኀብረተሰቡ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቅሰው የፀጥታ ኃይሉን በመደገፍ ሕገ ወጥ ተግባራት የሚያከናውኑትን ግለሰቦች አጋልጦ በመስጠት በኩል የሚደረገው ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል። በተጨማሪም በማንኛውም የኀብረተሰብ ክፍል ስም የሕዝብ ሰላምና ደህንነት የሚያውኩ እና ለውጡን ወደፊት እንዳይቀጥል የሚያደርጉ ሕገ ወጦች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም