በአማራ ክልል የደረሰውን የጉዳት መጠን ለመለየት እየተካሄደ ባለው ጥናት የ38 ከተሞች የመረጃ መሰብሰብ ስራ ተጠናቋል

ባህር ዳር፤ ጥር 21/2014 (ኢዜአ)፡ አሸባሪው ህወሓት በአማራ ክልል ያደረሰውን የጉዳት መጠን ለመለየት እየተካሄደ ባለው ጥናት በስድስት ዞኖችና በ38 ከተሞች የመረጃ ስብሰባ መጠናቀቁን የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ሃላፊ አቶ አንሙት በለጠ ለኢዜአ እንደገለጹት አሸባሪው ህወሓት ወረራ በፈፀመባቸው ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች ያደረሰውን የጉዳት መጠን በሳይንሳዊ ጥናት ለመለየት ከአንድ ወር በፊት መረጃ የማሰባሰብ ስራ ተጀምሯል።

የክልሉ መንግስት በአሸባሪው ህወሓት በሰባት ዞኖች የደረሰውን ውድመት እያጠና መሆኑን ጠቀስው፤ በ77 ከተሞች የደረሰው ጉዳት ደግሞ በማዕከላዊ ስታትስቲክ ኤጀንሲ እየተጠና እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በክልሉ መንግስት እየተካሄደ ባለው ጥናት 17 የክልሉ የቢሮ ተቋማት፣ የ10 የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች፣ከወረዳና ከቀበሌዎች የተውጣጡ ባለሙያዎችን ጨምሮ ከ2 ሺህ በላይ ባለሙያዎች እየተሳተፉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እስካሁንም በዋግ ህምራና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ ሰሜን ሽዋ፣ ደቡብ ጎንደር፣ ሰሜንና ደቡብ ወሎ ዞኖች የተካሄደ ባለው ጥናት መረጃ የመሰብሰብ ሂደቱ መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

የሰሜን ጎንደር ዞን መረጃ የመሰብሰብ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ አመላክተዋል።

የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ቤት ለቤት በመዘዋወር በ77 ከተሞች እያካሄደ ባለው ጥናት እስካሁን የደሴ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ የ38 ከተሞች መረጃ የማሰባሰብ ስራ መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

አሸባሪው ህወሓት በንጹሓን ዜጎችና በተለያዩ የመንግስትና የግል ተቋማት ላይ ጉዳት ማድረሱን የገለጹት አቶ አንሙት የጥናቱ ውጤት ይፋ ሲደረግ የጉዳቱን መጠን በዝርዝር ማወቅ እንደሚቻል አብራርተዋል።

በቀጣይ ይፋ የሚሆነው የጥናት ውጤት የደረሰውን የጉዳት መጠን በትክክል በመለየት ለመልሶ ግንባታና ማቋቋም ከፍተኛ ሚና እንዳለው አመልክተዋል።

በተጨማሪም ጉዳቱን ለታሪክ ሰንዶ ለማስቀመጥ ከሚኖረው ፋይዳ በላይ አሸባሪውን ህወሓት በተጨባጭ ማስረጃ በህግ ፊት ተጠያቂ ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ እየተካሄደ ላለው ጥናት የተሰባሰበውን መረጃ ወደ ኮምፒዩተር የማስገባት ስራ መጀመሩን አመልክተዋል።

በአጭር ጊዜ ውስጥ የመረጃ ትንተናውን በማጠናቀቅ የጥናቱ ውጤት በቀጣዩ ወር ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

አሸባሪው ህወሓት በአማራ ክልል በፈጸመው ወረራ በንጹሓን ዜጎች ላይ የሞት፣የአስገድዶ መድፈርና የአካል ጉዳት፣ የንብረት ዘረፋና ውድመት መፈጸሙ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም