አንድነታችንን አጠናክረን ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መልሶ ለመገንባት በጋራ መቆም አለብን - ኢዜአ አማርኛ
አንድነታችንን አጠናክረን ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መልሶ ለመገንባት በጋራ መቆም አለብን

ጥር 21/2014 (ኢዜአ) አንድነታችንን አጠናክረን ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መልሶ ለመገንባት በጋራ መቆም አለብን ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን ተናገሩ።
የገቢዎች ሚኒስቴር በ2013 የተሻለ የሥራ አፈጻጸም ላስመዘገቡ የተቋሙ ሰራተኞችና አመራሮች ዕውቅና እና ሽልማት ሰጥቷል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን፤ በመርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት መልእክትና የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል።
በመልእክታቸውም አገራዊ አንድነት በመገንባትና የኢትዮጵያን ሉአላዊነት በማስጠበቅ ረገድ ሁላችንም በጋራ መቆም አለብን ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች ሙሉ ለሙሉ ቆመዋል ማለት አይቻልም ያሉት አቶ ደመቀ አሁንም አንድነታችንን በማጥበቅ ለበለጠ ድል የምንሸጋገርበት ጊዜ መሆኑን አለበት ብለዋል።
በተለያየ አውድና መንገድ በጠብ አጫሪነት፣ በአቀነባባሪነትና አሳዛኝ የሆኑ ጥፋቶችን ለማስቀጠል የተዘጋጁ ሃይሎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
እነዚህን የጥፋት ዓላማ ያነገቡ ሃይሎች በዘላቂነት ለመመከትና አስተማማኝ ሰላም ለመገንባት አንድነትና የጋራ አሸናፊነታችን መቀጠል አለበት ብለዋል።
በአገር ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች ላይደገሙ የማክሸፍ፣ ስጋት እንዳይሆኑ መመከት ይገባል ያሉት አቶ ደመቀ የደረሱ ጉዳቶችን መልሶ የማልማትና የመገንባት ጉዳይም የጋራ ተግባራችን መሆን አለበት ነው ያሉት።
በዜጎች ላይ የደረሱ ስብራቶችን የመጠገን፣ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለአገልግሎት የማብቃት ስራ ላይ እንረባረብ ሲሉ አሳስበዋል።
በዚህ ወቅት ከተለያየ አቅጣጫ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን በመመከት በሁሉም የስራ መስኮች ውጤታማ መሆን ይገባል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ላይ ተደቅኖ የነበረው የህልውና ስጋት በሁሉም የጸጥታ ሃይሎችና በህዝቡ ትብብር የተቀለበሰበትን የአሸናፊነት መንገድ ጠብቆ በማስቀጠል በሌሎች ግንባሮችም ለስኬትና አሸናፊነት መረባረብ ይጠበቅብናል ሲሉ አሳስበዋል።
በዲፕሎማሲ፣ ምጣኔ ሃብት፣ በገቢ አሰባሰብና ሌሎችም አገራዊ ክንውኖች ለበለጠ ስኬት መስራት አለብን ነው ያሉት።
በግብር አሰባሰብ ሥርአቱ የታዩ አበረታች ጅምሮችን አጠናክሮ በመቀጠል ለአገር ልማትና እድገት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።