ወደ ውጭ ከተላኩ የተለያዩ ምርቶች ከ8 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

60

ደሴ፣  ጥር 21/2014--(ኢዜአ)-በአማራ ክልል በግማሽ ዓመቱ ወደ ውጭ ከተላኩ የኢንዱስትሪና ሌሎች ምርቶች ከ8 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ገቢ መገኘቱን የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ፡፡

ቢሮው ለሁለት ቀን በደሴ ከተማ ያካሄደው የበጀት አመቱ የስድስት ወራት የስራ እቅድ አፈጻጸም ግምገማ ተጠናቋል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ተፈሪ ታረቀኝ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ ከህልውና ዘመቻው ጎን ለጎን  የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማስፋት ጥረት ተደርጓል።

በበጀት አመቱ ስድስት ወራት ከወጭ ንግድ 16 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ ከ8 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ መገኘቱን ተናግረዋል።

ገቢው የተገኘው ለውጭ ገበያ ከተላኩ የኢንዱስትሪዎች፣ የማዕድንና የግብርና ምርቶችን ሽያጭ መሆኑን አመልክተዋል ።

በግማሽ አመቱ ለውጭ ገበያ ከተላኩ ምርቶች ውስጥ ጨርቃጨርቅና አልባሳት፣ የቆዳና ሌጦ፣ ማዕድን፣ አበባ፣ የቅባት እህሎች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል ።

ምርቶቹ ከተላኩባቸው አገራት መካከልም ጣልያን፣ ደቡብ አፍሪካና ቻይና ዋናዎቹ መሆናቸውን አመልክተዋል ።

በምስራቅ አማራ ክፍል በአሸባሪው ህወሓት ወራሪ ሀይል  ስር  በመቆየቱና በክፍሉ የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ጨምሮ ሌሎች ፋብሪካዎች  በወራሪው በመዘረፋቸውና በመውደማቸው ዕቅዱን ማሳካት አለመቻሉን ጠቁመዋል።

"ይሁን እንጂ ወራሪው ቡድን ባልደረሰባቸው የክልሉ ዞኖችና ወረዳዎች የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችና ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች አቅማቸውን አሟጠው እንዲሰሩ በመደረጉ የዕቅዱን ከግማሽ በላይ ማሳካት ተችሏል" ብለዋል።

"አሁን ላይ በአካባቢዎቹ የመጣውን አንጻራዊ ሰላም በመጠቀምና ችግሮችን በመፍታት በቀጣይ ስድስት ወራት የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማስፋት ይሰራል "ብለዋል።

በሰሜን ሽዋ ዞን የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ የኢንቨስትመንት ማስፋፊያና ኢንዱስትሪ ዞን ልማት ቡድን መሪ ወይዘሮ ትግስት ይገዙ በበኩላቸው በክልሉ የነበረው የጸጥታ ችግር ለዘርፉ በሚፈለገው መጠን ትኩረት እንዳይሰጥ ማድረጉን ገልጸዋል።

"በቀጣይ ከገቢ አንጻር በክልል ደረጃ  የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ኢንዱስትሪዎችን ጨምሮ አምራቾች በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ ይደረጋል" ብለዋል።

በመጋዘን የተከማቹ ምርቶች ወደ ገበያ እንዲወጡና አዳዲስ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ ገቢውን ለማሳደግ ጥረት እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም