ሁለተኛው አገር አቀፉ የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔትና ስራ ፕሮጀክት ትግበራ ማስጀመሪያ ስነስርዓት በድሬዳዋ እየተካሄደ ነው

147

ድሬደዋ፣  ጥር 21/2014 (ኢዜአ) በ550 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በጀት በአገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው ሁለተኛው ምእራፍ የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔትና ስራ ፕሮጀክት ትግበራ ይፋዊ ማስጀመርያ ስነ ስርአት በድሬዳዋ እየተካሄደ ነው።

ባለፉት አምስት አመታት በ450 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በአስራ አንድ ከተሞች የተተገበረው የመጀመሪያው ምዕራፍ ፕሮጀክት ተጠናቆ ሁለተኛው ምእራፍ ዛሬ በይፋ ተጀምሯል ።

የፕሮጀክቱ ተጠቃሚዎች በአገሪቱ ማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸው እንዲጎለብት ማገዙን እየተካሄደ ባለው የሁለተኛው ምእራፍ የፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ ስነስርዓት ላይ ተመላክቷል።

ዛሬ በድሬዳዋ “ልማታዊ ሴፍቲኔት ለከተሞች ሁለንተናዊ ለውጥ ” በሚል መሪ ሃሳብ በይፋ የሚጀመረው ሁለተኛው ምእራፍ የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔትና ስራ ፕሮጀክት በመጀመሪያው ምዕራፍ  ተጠቃሚ የሆኑትን 11 ከተሞች  ጨምሮ በ83 ከተሞች ተግባራዊ የሚደረግ ነው።

በአለም ባንክና በኢትዮጵያ መንግስት  በሚመደብ 550 ሚሊዮን ዶላር በሚተገበረው ሁለተኛው ምእራፍ ፕሮጀክት ከ816 ሺህ በላይ ሰዎች በቀጥታና በልማት ስራዎች በመሳተፍ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔትና ሥራ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ መኮንን ያኢ ለኢዜአ  

አስታውቀዋል።

በፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ ስነ ስርአት ላይ ላይ የፌደራል የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒን ጨምሮ የፌደራል፣ የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች  ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል ።

በዕለቱ በመጀመሪያው ምዕራፍ በድሬዳዋ የተገነቡ ፕሮጀክቶች የሚመረቁ ሲሆን በስነስርዓቱ ላይ የተሳተፉ እንግዶች በቀድሞው ባቡር ጉዞ እንደሚያደርጉ የወጣው መርሃ ግብር አመላክቷል።