ኢትዮጵያን በመገንባት ሂደት ዘላቂነት ድጋፍ ማድረግ የሚቻልበት ሁኔታ ለማመቻቸት ወደ አገር ቤት መጥተናል

209

ጥር 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን በመገንባት ሂደት ዘላቂነት ድጋፍ ማድረግ የሚቻልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ወደ አገር ቤት መምጣታቸውን የሰላምና አንድነት የዋሺንግተን ዲሲ ግብረሃይል አስተባባሪዎች ገለጹ።

ግብረሃይሉ የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር የሚያስችሉ የዲፕሎማሲ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

የሰላምና አንድነት የዋሺንግተን ዲሲ ግብረሃይል አስተባባሪዎች ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ የገቡ ሲሆን፤ በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በሚገኘው ጊዜያዊ የህክምና ቁሳቁሶች  ማከማቻ መጋዘን ድጋፍ አድርገዋል።

የግብረሃይሉ ዋና ሰብሳቢ አቶ ጣሰው መላከህይወት መልሶ ለማቋቋም የሚያስችሉ ድጋፎች እየተደረጉ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።

በቅርቡ በዋሺግንተን ዲሲ፣ ሜሪላንድና ቨርጂኒያ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ለተፈናቀሉ ዜጎች ከ300 ሺህ ዶላር ተሰብስቦ በ’አይዞን ኢትዮጵያ’ የበይነ መረብ የክፍያ አማራጭ ወደ አገር ቤት መላኩን አስታውሰዋል።

የግብረ ሃይሉ አባላት በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎችና ተቋማት በመመልከት በዘላቂነት የመልሶ ማቋቋም ሂደቱን ለመደገፍ የሚቻልበት ሁኔታ ላይ ይሰራል ብለዋል።

ግብረ ሃይሉ ሰላማዊ ሰልፎችን በማዘጋጀት፣ የአሜሪካ ባለስልጣናትን በማነጋርና ደብዳቤ በመጻፍ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር የሚያስችሉ የዲፕሎማሲ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝና ይሄን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም  ነው አቶ ጣሰው ያስረዱት።

የተለያየ እውቀትና ሙያ ያላቸው አባላት ኢትዮጵያን ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን የጠቀሱት የግብረሃይሉ አባል አቶ መስፍን አስፋው፤ ድጋፍ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከመንግስት የስራ ሃላፊዎች ጋር ለመነጋገር እቅድ እንደተያዘ አመልክተዋል።

ሌላኛዋ የግብረሃይሉ አባል ወይዘሮ ዘቢባ አህመድ በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን አገራቸውን ለመደገፍ ቆርጠው መነሳታቸውን ገልጸዋል።

መንግስት ድጋፍ ያስፈልገኛል በሚላቸው መስኮች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚደረግ  ተናግረዋል።

የሰላምና አንድነት የዋሺንግተን ዲሲ ግብረሃይል እ.አ.አ በ2011 የተቋቋመ ነው።

ግብረ ሃይሉ በቅርቡ በአሜሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲካሄዱ የነበሩ’ የበቃ’ ወይም #NoMore ሰላማዊ ሰልፎችን ሲያስተባብር እንደነበር ይታወቃል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼