አሸባሪው ህወሃት በአማራ እና አፋር ክልሎች ሙሉ ለሙሉ ያወደማቸው ትምህርት ቤቶች ደረጃቸውን ጠብቀው ይገነባሉ

127

ጥር 20/2014(ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት በአማራ እና አፋር ክልሎች ሙሉ ለሙሉ ያወደማቸው ትምህርት ቤቶች ደረጃቸውን ጠብቀው የሚገነቡ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተናገሩ።

አሸባሪው ህወሃት በአማራና አፋር ክልሎች በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች በድምሩ 1 ሺህ 93 ትምህርት ቤቶችን ሙሉ ለሙሉ ሲያወድም 3 ሺህ 220 የሚሆኑት ደግሞ መለስተኛ ጥገና የሚያስፈልጋቸው ናቸው።

በመሆኑም አሸባሪው ቡድን ሙሉ ለሙሉ ያወደማቸው ትምህርት ቤቶች ደረጃቸውን ጠብቀው የሚገነቡ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገልጸዋል።

በቡድኑ ሙሉ ለሙሉ ለወደሙት ትምህርት ቤቶች መልሶ ግንባታ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

ከግንባታው በተጨማሪም ለቁሳቁስ ግዥ 900 ሚሊዮን ብር ይጠይቃል ብለዋል።

የትምህርት ሚኒስቴር የሚገነቡትን ትምህርት ቤቶች በሚመለከት ከኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማሕበር ጋር ውይይት አድርጓል።

በዚህም የወደሙት ትምህርት ቤቶች ከቀድሞ በተሻለ ጥራትና ፍጥነት በሚገነቡበት ሁኔታ ላይ ተነጋግረዋል።

በሁለቱ ክልሎች በሽብር ቡድኑ የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለማቋቋም በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ከሁለቱ ከተማ አስተዳድሮችና ከአስሩ የክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች ጋር ምክክር መደረጉንም ገልፀዋል።

በመሆኑም ሁሉም አካላት በጦርነቱ ክፉኛ የተጎዱ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባትና ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታቸው ለመመለስ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ጠቁመዋል።

ከዚህም  የገንዘብ፣ የቁሳቁስ አና የአይነት ድጋፍ ለማድረግ የቢሮ ኃላፊዎቹ ስምምነት ላይ ደርሰዋል ነው ያሉት። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም