በቄለምና ምዕራብ ወለጋ በፀጥታ ችግር ምክንያት የተራዘመው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ሊሰጥ ነው

176

ጊምቢ፣ ጥር 20/2014 (ኢዜአ)–በቄለምና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች በፀጥታ ችግር ምክንያት የተራዘመው የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ መልቀቂያ ፈተና በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚሰጥ የዞኖቹ ትምህርት ጽህፈት ቤቶች አስታወቁ።

የጽህፈት ቤቶቹ  ኃላፊዎቹ ለኢዜአ እንደገለጹት ፈተናው በቄለም ወለጋ 12 ወረዳዎችና በምዕራብ ወለጋ ዞን ሁለት ወረዳዎች ከጥር 23 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ይሰጣል።

ፈተናው ያለ አንዳች የፀጥታ ስጋት  እንዲሰጥ በየደረጃው የሚገኙ  የፀጥታና በሚመለከታቸው አካላት በቂ ዝግጅት መደረጉንም አስታውቀዋል።

በቄሌም ወለጋና በምዕራብ ወለጋ ዞኖች በሚሰጠው ፈተና ከ16 ሺህ 600 በላይ ተማሪዎች እንደሚፈተኑ ኃላፊዎቹ ገልጸዋል።

የቄሌም ወለጋ ዞን ትምህርት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ኤፍሬም ተፈራ እንደገለጹት በዞኑ በሚገኙ 12 ወረዳዎች 14ሺህ 540 ተማሪዎች ለፈተና ይቀመጣሉ።

ለዚህም 42 የፈተና ጣቢያዎች መዘጋጀታቸውንና ለፈተናው አስፈላጊ የሆኑ  ግብዓቶች  መሟላታቸውን ተናግረዋል።

የምዕራብ ወለጋ ዞን ትምህርት ቤቶች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮናስ እምሩ በቤጊና ቆንዳላ ወረዳዎች ከ2 ሺህ በላይ ተማሪዎች በመንዲ ከተማ ለፈተና ይቀመጣሉ።

ፈተናውን ለመስጠት የሚያስችሉ አራት የፈተና ጣቢያዎች መዘጋጀታቸውን አቶ ዮናስ ገልጸዋል።