የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የጂኦ ስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ሥምምነት ተፈራረሙ

251

ጥር 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የጂኦ ስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የጂኦ ስፓሻል (የመሬት) መረጃ ለመለዋወጥና በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸው የመግባቢያ ሥምምነት በዛሬው እለት ተፈራርመዋል፡፡

የመግባቢያ ሰነዱን የፈረሙት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አሸብር ባልቻ እና የጂኦ ስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲቱዩት ዋና ዳሬክተር  ዶክተር ቱሉ በሻ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አሸብር ባልቻ በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ  እንደተናገሩት፤ ተቋሙ ለሚያከናውነው ሥራ የጂኦ ስፓሻል ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው።

ቴክኖሎጂውን በአግባቡ መጠቀም ወጪ ቆጣቢ በሆነ  መልኩ ለመስራት እና በተገቢው ሁኔታ ለማስተዳደር  ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል ፡፡

የትብበር ስምምነቱ በሀገር ውስጥ ያለውን አቅም አስተባብሮ  ተቀራርቦ በመስራት የሀገር ሀብትን  በተገቢው ሁኔታ  ለመጠቀም፣  የእውቀት ሽግግርና የአቅም ግንባታ ሥራዎችን በሁለቱ ተቋሟት ለማስፋፋት ጠቀሜታው የጎላ  ነው ብለዋል።

ሥምምነቱ ሁለቱ ተቋማት በመረጃ ልውውጥ፣ በቴክኖሎጅ ሽግግር፣ በምርምርና ልማት በሚያከናውኗቸው ፕሮጀክቶች ላይ በጋራ ለመስራት እንደሚያስችል ተገልጿል፡፡

የጂኦ ስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቱሉ በሻ በበኩላቸው የኃይል ዘርፉን መሰረተ ልማት ማዘመን ኢትዮጵያ በቀጣይ 10 ዓመታት ለማሳካት ላቀደቸው ሁለተናዊ እድገት ቁልፍ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡

በመሆኑም ተቋማቸው ያለውን የካበተ ልምድ ለማካፈል እና አብሮ ለመስራት መቻሉ የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንደሚያግዝ ገልጸዋል። 

የትብብር ስምምነቱ ከኢነርጂ ተደራሽነት ጋር በተያያዘ የብሔራዊ የሀብት ጠቋሚ መረጃ፣ የብሔራዊ የመሰረተ ልማት የመረጃ ልውውጥ፣ የሶፍት ዌር ማበልፀግና የኢንፎርሜሽን ደህንነት አገልግሎት፣ የስልጠናና ልምድ ልውውጥ፣ የሳይንሳዊ ዕውቀት፣ የቴክኖሎጂ እና መረጃ ልውውጥ እንዲሁም ውጤታማ የጂኦ ስፓሻል መረጃ አያያዝና አተገባበር ላይ በጋራ ለመስራት እንደሚያስችል ተጠቁሟል፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼