በቦረና ዞን የድርቅ ተፅእኖ ያስከተለውን ችግር ለመቋቋም የመንግስትና ግብረሰናይ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲቀጥል ተጠየቀ

108

ጥር 20/2014(ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን የድርቅ ተፅእኖ ያስከተለውን ችግር ለመቋቋም በመንግስትና ግብረሰናይ ድርጅቶች የሚደረገው ድጋፍ ቀጣይነት እንዲኖረው ተጠየቀ።

የኢዜአ ሪፖርተር በቦረና ዞን ሞያሌ ወረዳ ጢሌ መዶ እና ቤዴ በተባሉ ቀበሌዎች አርሶ አደሮችን ተዘዋውሮ አነጋግሯል።

በአካባቢው የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ በመንግስትና አንዳንድ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ለሰዎች ምግብና የእንስሳት መኖ ድጋፍ መደረጉን አስታውሰዋል።

የድርቁ ተፅእኖ አሁንም ተባብሶ በመቀጠሉ በተለይም በእንስሳት ላይ ሞት እያስከተለ መሆኑን ገልጸው ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የሞያሌ ወረዳ የአደጋ ስጋት እና የልማት ተነሺዎች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጎጂ አሬሮ፤ የድርቁን መከሰት ተከትሎ እስካሁን በአራት ዙር ለሰው ደራሽ ምግብና ለእንስሳት መኖ ተደራሽ ተደርጓል ብለዋል።

በመንግስትና በግብረሰናይ ድርጅቶች ለእንስሳት 1 ሺህ 379 ኩንታል ፉርሽካ እና የሳር አቅርቦት ተደርጓል ነው ያሉት።

ከ9 ሺህ 700 ለሚልቁ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰው ሆኖም በአካባቢው የተከሰተው ድርቅ ተባበሶ በመቀጠሉ ተጨማሪ ድጋፍና እገዛ ያስፈልጋል ብለዋል።

ከመንግስት በተጨማሪ ሌሎች የግብረሰናይ ድርጅቶች እና አጠቃላይ ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ በማድረግ አጋርነታቸውን እንዲያሳዩ ጠይቀዋል።

የሞያሌ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ኢብራሂም አብዲ፤ የድርቁ ሁኔታ አሳሳቢ ሆኖ መቀጠሉን ገልጸው የተጠናከረና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል።

የኦሮሚያ አደጋ ስጋትና ተነሽዎች ልማት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ገረሙ ኦሊቃ፤ የአደጋ ተጋላጭነታቸው በተለዩ አካባቢዎች የድጋፍና እገዛ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ምክትል ኮሚሽነር ገለፃ ምስራቅ ሀረርጌ፣ ምዕራብ ሀረርጌ፣  ሰሜን ሸዋ፣ ቦረና እና ባሌ ዞኖች የአደጋ ተጋላጭነታቸው ቀድሞ ተለይቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም