በሕዝቦች መካከል ሠላም እና አንድነት ለማጠናከር ኪነ-ጥበብ ትልቅ መሳሪያ ነው

95

ጥር 20 ቀን 2014(ኢዜአ) ኪነ-ጥበብ በሕዝቦች መካከል ሠላም እና አንድነትን ለማጠናከር፤ የሃሳብ ተቃርኖዎችንም ለማስታረቅ ትልቅ መሳሪያ ነው ይላሉ አንጋፋው የጥበብ ባለሙያ አያልነህ ሙላት።

ኪነ-ጥበብ በሰው ልጆች የዕለት ተዕለት የሕይወት መስተጋብር ውስጥ ልማትና ጥፋት፣ሰናይ እና እኩይ ሃሳቦችን በማይጠፋ አሻራ የማስተላለፍ አቅም ካላቸው ዘርፎች መካከልም አንዱ ነው።

የጥበብ ሃብት በታደለችው ኢትዮጵያም በታሪክ፣ በባሕል ብሎም ወቅቱን ጠብቀው በሚካሄዱ ትውፊታዊ ክንዋኔዎች ሕዝቦችን የማቀራረብ፣ ሠላምና አንድነትን የማጠናከር ሥራዎች ሲሰሩበት ቆይቷል።

ኢትዮጵያ በቅርቡ በውስጥና በውጭ ኃይሎች በተከፈተባት ጥቃት ምክንያት ሠላምና ጸጥታዋ እንዲደፈርስ ብሎም ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መዛባቶች አጋጥመዋታል።

እንዲህ ባለው ጊዜ ታዲያ ኪነ-ጥበብ ኢትዮጵያዊነትን፣ አንድነትን በሚሰብኩ ሥራዎች በሐሳብ የተለያየን ሕዝብ ወደ አንድነት የማምጣት አቅም ያለው መሣሪያ ነው ሲሉ ነው አንጋፋው የጥበብ ባለሙያ አያልነህ ሙላት የገለጹት።

ኪነ-ጥበብ በአገር ግንባታ ረገድም ሕዝቦችን ለልማት ማነሳሳት እንደሚችል ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያዊያን እና የአጎራባች አገራት ሕዝቦች በኪነ-ጥበብ ዓለም የተዋሃዱ ናቸው የሚሉት የጥበብ ባለሙያው፤ ኪነ-ጥበብ የሐሳብ ተቃርኖንም የማስታረቅ ሚና እንዲጫወት ማድረግ ይቻላልም ብለዋል።

በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በባህል እና በሌሎችም መስኮች ግንባር ቀደምም አስተማሪም ነው ብለዋል።

በመሆኑም ለአገር ሠላም እና ለሕዝቦች አንድነት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ በመገንዘብ የኪነ-ጥበብ ዘርፉን ማበረታታት እና መደገፍ ያስፈልጋል ሲሉ አመልክተዋል።

በሌላ በኩል የዘርፉ ባለሙያዎችም ለአገራዊ ሠላም፣ለሕዝቦች አንድነትና ልማት ሙያዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ 

‼️

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼️

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼️

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼️
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም