ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ለአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ስኬት በጋራ እንዲቆሙ ጥሪ አቀረቡ

200

ጥር 20 ቀን 2014 (ኢዜአ)ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ለአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ስኬት በጋራ እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

“መላው የከተማችን ነዋሪዎች፤ በአፍሪካዊነታችን እየኮራን ለአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ስኬት በጋራ እንቁም” ብለዋል ከንቲባዋ፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ “ከተማችን አዲስ አበባ የአፍሪካዊያን መዲና ፤ የአለም የዲፕሎማቲክ ማዕከል የህብረብሄዊነት አርማ ነች” ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዘመናት ውስጥ ለመላ አፍሪካውያን ድምፅ በመሆን በተደጋጋሚ ለአፍሪካውያንና ለፓን-አፍሪካኒዝም አስተሳሰብ ትልቁን የመሪነት ሚና ስትጫወት የነበረች የአፍሪካውያን የአሸናፊነት ተምሳሌት መሆኗን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል፡፡

“አፍሪካውያን ወደ ቤታቸው የሚሰበሰቡበት ይህ ጉባኤ ሁላችንም በጉጉት የምንጠብቀው በተለይም በዚህ ወቅት ለኢትዮጵያ ብሎም ለከተማችን አዲስ አበባ ልዩ ትርጉም ያለው ነው” ብለዋል ከንቲባዋ፡፡

ከንቲባ አዳነች፣ ኢትዮጵያ ገጥሟት ከነበረው ውስጣዊና ውጫዊ የህልውና ትግል አንፃር ጉባኤው ለኢትዮጵያ የመልካምና የአሸናፊነት ማብሰርያ ነው ብለዋል፡፡

“በተደረገው ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጥረት ፤አፍሪካዊያን ወንድሞቻችንም ከጎናችን መሆናቸውን ጉባኤው እንዲካሄድ በመወሰን ያሳዩበትና ፤ ለሃገራችን ያላቸውን አክብሮትና ወዳጅነት ያረጋገጡበትም ነው” ብለዋል ከንቲባዋ፡፡

ጉባኤው ኢትዮጵያ ሰላም አይደለችም፤ በርካታ የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ ሊታደሙባት ቀርቶ ፤ያሉትም የውጪ ዜጎች ከተማዋን ለቀው መውጣት አለባቸው በማለት በከፍተኛ ደረጃ ሲካሄድ የነበረውን የሚድያ ዘመቻ በማጋለጥ ፤ እውነትም ኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላም በራሷ ማረጋገጥ የምትችል መሆኗን፤ ከተማችን አዲስ አበባም ከምንጊዜውም በላይ ሰላማዊና ውብ እንደወትሮውም የአፍሪካውያን መዲና ሆና መቀጠል የሚያስችል ብቃት ያላት መሆኑን ያረጋገጠ ጭምር ነው ብለዋል ከንቲባ አዳነች፡፡

“ጉባኤው ለከተማችንም ይሁን ለሃገራችን ሌሎችም ብዙ ትርጉሞች ያሉት ጉባኤ ነው፡፡ ስለሆነም ለዚህ ጉባኤ ስኬታማነት ሁላችንም ትልቅ ሃላፊነት አለብን”ብለዋል፡፡

አዲስ አበባ ከተማ ይህንን ታሪካዊ ጉባኤ በደመቀና ባማረ መልኩ ተካሂዶ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጓን ከንቲባዋ ገልፀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የፊታችን እሁድ በሚካሄደው ከተማ አቀፍ የፅዳት ፕሮግራም ላይ ያለማንም አስተባባሪና ያለማንም ቀስቃሽ በራሱ ወጥቶ አካባቢውንና ሰፈሩን እንዲያፀዳና እንዲያሳምር ከንቲባዋ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

“ውድ ባለሃብቶቻችንም በየአካባቢው ህንፃዎችን እንድታሸበርቁና የውስጥና የውጪ መብራቶችን ባለማጥፋት ለከተማው ድምቀት የበኩላችሁን እንድትወጡ አደራ እላለሁ” ብለዋል ከንቲባ አዳነች፡፡

“በክፉ ቀን ከተማችንን በመታደግ ትልቅ ሚና የተወጣችሁ ህዝባዊ ሰራዊቶቻችን በየአካባቢው ሰላማችንን በመጠበቅ ፤ ባህላችንን ገፅታችንንና ህብረብሄራዊ ቀለማችንን በማስተዋወቅ ፤ ከፀጥታ ሃይሎች ጋር በመተባበርና ተጋግዞ በመስራት ይጠበቅባችኋል፡፡አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም ከወትሮው በተለየ ሁኔታ የሚጠበቅብንን ሁሉ ብቁ አገልግሎት በመስጠት ሃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል” ብለዋል ፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ “መላው የከተማችን ነዋሪ በተለመደ ኢትዮጵያዊ ጨዋነትና እንግዳ ተቀባይነት እንግዶቹን በማስተናገድ ወደ መዲናችን የሚመጡ አፍሪካውያን ወደ ቤታቸው እንደመጡ ሆኖ እንዲሰማቸው በማድረግ ሃላፊነቱን እንዲወጣ አደራ እላለሁ” ብለዋል፡፡