የሸማቹን መብት የሚያከብር ጤናማ የንግድ ስርዓት ለመፍጠር ቅንጅታዊ አሰራሮችን መከተል ያስፈልጋል

128

ሶዶ ጥር 19/2014-(ኢዜአ) -የሸማቹን መብት የሚያከብር፣ ዘመናዊና ጤናማ የንግድ ስርዓት ለመፍጠር ቅንጅታዊ አሰራሮችን መከተል ያስፈልጋል ሲሉ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተስፋዬ ይገዙ አስገነዘቡ።

በክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የተዘጋጀውና የንግድ ስርዓቱን ማዘመንና የሸማቾችን መብት ማስከበርን ዓላማ ያደረገ የምክክር መድረክ በወላይታ ሶዶ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተስፋዬ ይገዙ በወቅቱ እንዳሉት በገበያ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሸማቹን መብት የሚያከብር የንግድ ማህበረሰብ መፍጠር ያስፈልጋል።

“ስግብግብ ነጋዴዎች ትርፋቸውን አስቀድመው ጥራት የጎደለው ምርት ሲሸጡ በዜጎች አካልና ስነልቦና እንዲሁም በአገር ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ጉዳት እንዳለው ሊገነዘቡ ይገባል” ሲሉ ገልጸው የተረጋጋ፣ ዘመናዊና ጤናማ የንግድ ስርዓት ለመፍጠር የሚመለከታቸው አካላት በተቀናጀ መልኩ ሊንቀሳቀሱ ይገባል።

በንግድ ስርዓቱ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን የንግድ አዋጁ በሚፈቅደውና አሳታፊ በሆነ መልኩ ተገቢ እርምጃ በመውሰድና በዘላቂነት መፍታት እንደሚገባ ተናግረውም የፍትህ አካላትን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት በተቀናጀና በተደራጀ አግባብ በመንቀሳቀስ ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል።

ሀገር ችግር በገጠማት ወቅት ያላግባብ ለመክበር የፈለጉ ነጋዴዎች ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ሲያደርጉና ምርት ሲደብቁ መስተዋሉን የገለጹት ደግሞ የደቡብ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ማሄ ቦዳ ናቸው።

ድርጊቱን ስርአት ለማስያዝና የሸማቹን ማህበረሰብ መብት ለማስከበር ቢሮው የተለያዩ ተግባራት ማከናወኑንና የሸማቹን መብት ያስከበረ ጤናማ የንግድ ስርዓት ለመዘርጋት የተጠናከረ ሥራ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

“ሸማቹ መብቱ ተጠብቆ እንዲገበያይ በሃላፊነት ስሜት መስራት ይኖርብናል” ያሉት ሃላፊው ሸማችና አምራቹ የሚገናኙበትን ሰንሰለት ማሳጠር እንደሚገባ አመልክተዋል።

በየአካባቢው ያሉ ህገወጥ ደላሎችን የመቆጣጠርና ሕብረት ሥራ ማህበራትን የማበረታታት ሥራ እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረው ባለፉት 6 ወራት ጥራታቸው የተጓደለና ጊዜ ያለፈባቸውን ምርቶች ለሽያጭ ያቀረቡ ከ29 ሺህ በላይ ነጋዴዎችን በህግ ተጠያቂ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።