ግብረ ሰናይ ድርጅቱ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የምግብ ድጋፍ አደረገ

117

ባህር ዳር (ኢዜአ) ጥር 19/2014—በአሜሪካን አገር የሚገኘው “ኤ ብራይት ፊውቸር ፎር ኪድስ” የተባለ ግብረሰናይ ድርጅት በአማራ ክልል በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚውል ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የምግብ ድጋፍ አደረገ።

የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰሎሞን ዳቤ በርክክብ ስነ ስርዓቱ ላይ እንዳሉት አሸባሪው ህወሓት  የፈጸመው ወረራና ግፍ ሁሉም ዳያስፖራ በአንድነት እንዲነሳና ለአገሩ እንዲቆም አድርጓል።

በሚኖሩበት አሜሪካን አገር ያሉ ድርጅቶችን በማስተባበር ከ32 ነጥብ 5 ኩንታል በላይ አልሚ ምግብና 500 ሊትር ዘይት ድጋፍ  ይዘው መምጣታቸውን ገልጸዋል።

አልሚ ምግቡ በአሜሪካን አገር የጥራት ደረጃና ሁሉንም ንጥረ ነገሮች አሟልቶ የተመረተ በመሆኑ ለህጻናትና እናቶች ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

“በአማራ ክልል የደረሰውን ሰብአዊ፣ ቁሳዊና ስነ ልቦናዊ ጉዳት ተዘዋውሬ አይቻለሁ” ያሉት አቶ ሰለሞን በቀጣይም በእለት ምግብና መልሶ ማቋቋም ሥራ ድርጅቱ የተጠናከረ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።  

የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን የቅድመ ማስጠንቀቂያ ምላሽ ዳይሬክተር አቶ ጀምበሩ ደሴ በበኩላቸው፣ በክልሉ ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ተፈናቃዮች እንደነበሩ አስታውሰዋል።

በደባርቅ እና ዳባት የሚገኙ ከ133ሺህ በላይ ተፈናቃዮችን ሳይጨምር ሌሎቹን ወደአካባቢያቸው በመመለስ ባሉበት የመደገፍ ሥራ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

አቶ ጀምበሩ እንዳሉት ለተፈናቃዮች በፌደራል መንግስትና በሌሎች ረጅ ድርጅቶች እየተደረገ ያለው ድጋፍ ስንዴ፣ ዱቄትና ዘይት ብቻ በመሆኑ የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ላይ እጥረት አለ።

“በአሜሪካ የሚገኘው ድርጅት ያመጣው አልሚ ምግብ ለተጎዱ ህጻናትና እናቶች በሚቀርበው የተመጣጣነ ምግብ ላይ ያለውን ክፍተት ለመሙላት ያግዛል” ሲሉም ገልጸዋል።

በክልሉ አሸባሪው የህወሓት ቡድን በፈጸመው ወረራ በአጠቃላይ ከ11 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ህዝብ እርዳታ እንደሚፈልግ ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።