በመዲናዋ ባለፉት ሶስት ዓመታት የተገነቡ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ለአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ መስተንግዶ ተጨማሪ ድምቀት ይሆናሉ

125

አዲስ አበባ፣  ጥር 19/2014(ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት ሶስት ዓመታት የተገነቡ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ለአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ መስተንግዶ ተጨማሪ ድምቀት እንደሚሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ ሜጋ ፕሮጀክቶች ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

ኢትዮጵያ በውስጥና በውጭ የገጠማትን ጫናዎች ተቋቁማ 35ኛውን የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ለማስተናገድ ዝግጅቷን አጠናቃ፤ እንግዶቿን እየተጠባበቀች ትገኛለች፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ሜጋ ፕሮጀክቶች ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ደቦ ቱንካ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በመዲናዋ ባለፉት ሶስት ዓመታት የከተማዋ ገጽታ የቀየሩ ትላልቅ ፕሮጀክቶች እውን ሆነዋል፡፡

የወዳጅነት አደባባይ ፣የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት፣ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ህንጻ እድሳት፣ የአብርሆት ቤተ መጻህፍት፣ መስቀል አደባባይ ማዘጋጃ ቤት ፕሮጀክት እና ሌሎች ከተማዋን ለማስዋብ የተከናወኑ ፕሮጀክቶችን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ አሸባሪው ህወሃትን ጨምሮ በውስጥና በውጭ ጠላቶች ተደቅኖባት የነበረውን የህልውና አደጋ ቀልብሳ ጉባኤውን ለማዘጋጀት መብቃቷ ደግሞ ጥንካሬዋን ያሳያል ነው ያሉት፡፡

በዚህም አፍሪካውያን ወንድሞቻችን ጉባኤውን በአዲስ አበባ ለማዘጋጀት ወስነው መምጣታቸው አፍሪካዊያን የትኛውንም ችግር በትብብር ማለፍ እንደሚችሉ ያመላከተ ነው ብለዋል፡፡    

ኢትዮጵያ ባለፉት ሶስት ዓመታት እውን ያደረገቻቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች አፍሪካን በትብብርና የትውልድ ቅብብሎሽ መገንባት እንደሚቻል ማሳያ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቶቹ አዲስ አበባን ልዩ ውበት በማላበስ የህብረቱን የመሪዎች ጉባኤ ተጨማሪ ድምቀት እንደሚሆንም ነው የተናገሩት፡፡

እንደ ዋና ስራ አስኪያጁ ገለጻ፤ በአዲስ አበባ ከሚገኙ 7 ትላልቅ ፕሮጀክቶች መካከል 3 ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት የጀመሩ ሲሆን አራቱ በእቅዳቸው መሰረት እየተከናወኑ ይገኛሉ።

በተጨማሪም ለከተማዋ እድገት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው የዲዛይንና የኮንትራት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም