ህብረተሰቡ በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ ያለውን ግንዛቤ በማሳደግ ረገድ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለፀ

62
ሃዋሳ ግንቦት 9/2010 በደቡብ ክልል በሚገኙ ሀይቆች፣ ወንዞችና ከተሞች ላይ እየደረሰ ያለውን ብክለት ለመከላከል የመገናኛ ብዙሃንና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች የህዝቡን ግንዛቤ ከማሳደግ አንጻር በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡ የደቡብ ክልል የአካባቢ ጥበቃና ደን ባለስልጣን በክልሉ ከሚገኙ መገናኛ ብዙሀንና ሴክተር መስሪያ ቤቶች ለተውጣጡ የመገናኛ ብዙሃንና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች በጉዳዩ ዙሪያ ያዘጋጀው የሦስት ቀናት ስልጠና በመካሄድ ላይ ነው፡፡ የባለስልጣኑ የአካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ዳይሬክተር አቶ በላይነህ ባራሞ ትናንት በተጀመረው ስልጠና ላይ እንዳሉት ከከተሞች መስፋፋትና እድገት ጋር ተያይዞ የተለያዩ ኢንደስትሪዎች፣ የጤና ተቋማት፣ ሆቴሎችና መኖሪያ ቤቶች የሚወጣው ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ መጠን እየጨመረ ነው፡፡ ከድርጅቶችና ተቋማት የሚወጣው ደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ ወደ ሀይቆችና ወንዞች በመቀላቀል እያደረሰ ያለው ብክለት አሳሳቢና ለጤና አስጊ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ ህብረተሰቡ በቆሻሻ አወጋገድ ዙሪያ ተገቢውን ግንዛቤ አግኝቶ በሀይቆች፣ ወንዞችና ከተሞች ላይ እያደረሰ ያለውን ብክለት እንዲከላከል ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡ ከዚህ አንጻር የሚታየውን ክፍተት ለመሙላት የመገናኛ ብዙሃንና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ከህዝቡ ጋር ያላቸው ቀረቤታ በመጠቀም ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ በባለስልጣኑ የአካባቢ ብክለት ትንተናና ቁጥጥር ባለሙያ አቶ ተፈራ ማተቤ በበኩላቸው የክልሉ ከተሞች ከቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ችግር እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡ ከደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ጋር በተያያዘ የሚፈለገውን ያህል ባይሆንም በሀዋሳ የተሻለ አሰራር መኖሩን ገልፀው በሌሎች ከተሞች ከመኖሪያ ቤት፣ ከተቋማትና ድርጅቶች የሚወጣ ቆሻሻ የሚጣለው በትክክለኛ ቦታው እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ ለብክለቱ ምክንያት የሚሆኑ ነገሮችን በመለየትና በካይ ፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ የሚለቁ ተቋማትን ተከታትሎ በማጋለጥ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ በማድረግና ለህዝቡ ግንዛቤ ከመፍጠር አንጻር የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡ ባለሙያዎች እንደ ሌሎቹ የልማት ስራዎች ሁሉ የአካባቢ ጥበቃንም እንደ አንድ አጀንዳ በመያዝ ተከታታይ ዘገባዎችን መስራት እንዳለባቸው ገልፀው ባለስልጣኑም በዚሁ ዙሪያ ከመገናኛ ብዙሀን ጋር በትብብር ለመስራት በማሰብ ስልጠናው መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ የደኢህዴን ልሳን ጋዜጠኛ ጌቱ ሻንቆ በሰጠው አስተያየት ከኢንደስትሪዎች ከመኖሪያ ቤቶችና ከተለያዩ ተቋማት የሚጣለው ቆሻሻ እያደረሰ ያለው ጉዳት በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል የመገናኛ ብዙሃን ያለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ በጉዳዩ ዙሪያ ዘገባዎችን ለመስራት ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላም በራቸውን ክፍት ሊያደርጉ እንደሚገባ ጠቁሟል፡፡ የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ የሆኑት አቶ አረጋዊ ሲማ በበኩላቸው ''በክልሉ ቆሻሻ እያደረሰ ያለው ብክለት አሁን ሊታይ ባይችልም ነገ ይዞ ሊመጣ የሚችለውን አስከፊ አደጋ በማሰብ ከወዲሁ ሊሰራ ይገባል'' ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም