የጸጥታ መዋቅሩን በማጠናከር ድንበር ዘለልና ሌሎች ወንጀሎችን ለመከላከል እየተሰራ ነው

176

ጋምቤላ፣ ጥር 19/2014(ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል የጸጥታ መዋቅሮችን በማጠናከር ድንበር ዘለልና ሌሎች ወንጀሎችን ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ኡቶ ኡኮት ለኢዜአ እንደገለጹት ክልሉ ሰፊ የድንበር ወሰን ያለው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በድንበር ዘለል ዘራፊዎችንና አርብቶ አደሮች እየተከሰቱ የሚገኙ ወንጀሎችን ለመከላከል አስፈላጊው የጸጥታ አካላት ስምሪት ተደርጓል።

በተለይም የሙርሌ ጎሳ በበጋ ወራት ድንበር አልፎ በመግባት ህፃናትን አፍኖ የመውሰድና የቀንድ ከብቶች ዘረፋ እንደሚፈጸም ገልጸዋል።

ጎሳው በቅርቡ በአኝዋክና በኑዌር ዞኖች በፈጸመው ወረራ 11 ሰዎችን በመግደል፣ በአራት ሰዎች ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት ማድረሱንና አምስት ህፃናትን አፍኖ መውሰዱንም አስታውቀዋል።

ከ100 በላይ የቀንድ ከብቶችን እንደዘረፈም ምክትል ቢሮ ኃላፊው ገልጸዋል።

በጎሳው እየተፈጸሙት ያሉትን ወንጀሎች ለመከላከል ስምሪት መደረጉንና የጎሳ አባላቱ ከሚመጡበት አስተዳደር ጋር በመወያየት ችግሩን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በየዓመቱ የበጋው ወራት ከጎረቤት አገር የቀንድ ከብቶች ይዘው የሚመጡ የፈላታ አርብቶ አደሮች ወደ ክልሉ እንዳይገቡ ለመከላከል ዝግጅት ማድረጉን አስታውቀዋል።

የሙርሌ ጎሳ በክልሉ ከስድስት ዓመታት በፊት  ከ200 በላይ ሰዎች ላይ ግድያ በመፈጸም፣ ከ135 በላይ ህፃናት አፍኖ በመውስድና ከ2 ሺህ በላይ የቀንድ ከብቶችን መዝረፉ ይታወሳል።