በአሸባሪው ህወሃት ጉዳት ከደረሰባቸው ኢንዱስትሪዎች መካከል 27ቱ ማምረት ጀምረዋል

383

ጥር 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአሸባሪው የህወሃት ቡድን ጉዳት ከደረሰባቸው ኢንዱስትሪዎች መካከል 27ቱ ማምረት መጀመራቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ገለጹ፡፡

ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮዎች የስራ ኃላፊዎች አሸባሪው ህወሃት በደሴና ኮምቦልቻ በሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ላይ ያደረሰውን ጉዳት ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በወቅቱ እንደገለጹት፤ ጉብኝቱ በዋናነት በሪፖርት የሚገለጹ መረጃዎችን በአካል በመመልከት መፍትሄ ለመስጠት ያለመ ነው፡፡

በጉብኝቱ አሸባሪው ህወሃት ኢንዱስትሪዎችን ብቻ ሳይሆን በቀጣይ ወደ ስራ ለመግባት የተዘጋጁ ድርጅቶችን ጭምር ማውደሙን መመልከታቸውን ተናግረዋል።

ቡድኑ በኢንዱስትሪዎች ላይ ከፈጸመው ዝርፊያ ባሻገር ከፍተኛ ውድመት ማድረሱንም ተናግረዋል።

ይህም የኢንዱስትሪ ልማቱ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እንዳይደግፍ ለማድረግ ሆነ ተብሎ የተፈጸመ ተግባር መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

አሸባሪ ቡድኑ በአጠቃላይ 82 በማምረት ላይ የነበሩና 5 በግንባታ ሂደት ላይ ያሉ ኢንዱስትሪዎች ላይ ውድመትና ዝርፊያ መፈጸሙን ገልጸው፤ ከእነዚህ መካከል 27ቱ ማምረት መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

እነዚህ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ ቢመለሱም የጥሬ እቃ፣ የመስሪያ ካፒታል እና የመለዋወጫ ችግር እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡

ስራ የጀመሩ ኢንዱስትሪዎች በመሉ አቅማቸው ወደ ምርት እንዲሸጋገሩና ስራ ያልጀመሩት ደግሞ እንዲጀምሩ ሚኒስቴሩ ዝርዝር ጥናት አካሂዶ ለሚመለከታቸው አካላት ማስተላለፉን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼