አሸባሪው ህወሓት ከ3 ሺህ በላይ የህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒየኖች ላይ ዘረፋና ውድመት አድርሷል

136

ባህር ዳር ፣ ጥር 19/2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል አሸባሪው የህወሓት ቡድን 3 ሺህ 228 የህብረት ስራ ማህበራትንና ዩኒየኖችን መዝረፉንና ማውደሙን የክልሉ የህብረት ስራ ማህበራት ማስፋፊያ ኮሚሽን አስታወቀ።

የሽብር ቡድኑ በህዝብ ሀብትና ንብረት ላይ ያደረሰው ዘረፋና ውድመትም ወደ 25 ቢሊዮን ብር እንደሚገመት ኮሚሽኑ ገልጿል።

የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ልጃለም ገዳሙ ለኢዜአ እንደገለጹት አሸባሪው ህወሓት በክልሉ ወረራ ፈጽሞ በቆየባቸው ሰባት ዞኖች በህዝብ ሀብትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ዘረፋና ውድመት ፈፅሟል።

የሽብር ቡድኑ ዘረፋና ውድመት ያደረሰው በ3 ሺህ 127 መሰረታዊ የህብረት ስራ ማህበራት፣ በ22 ዩኒየኖችና በ79 የዞንና ወረዳ ህብረት ስራ ማህበራት አደራጅ ጽህፈት ቤቶች ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኃላፊው እንዳሉት የሽብር ቡድኑ በህብረት ስራ ማህበራቱ መጋዝኖች ተከማችቶ የነበሩ የተለያየ የሰብልና የሸቀጣ ሸቀጥ ምርቶች፣ የአፈር ማዳበሪያና የፀረ ሰብል ተባይና አረም ኬሚካሎች ይገኙባቸዋል።

እንዲሁም ስምንት የእርሻ ትራክተሮችን ጨምሮ በርካታ የመስክ ተሽከርካሪዎች፣ ማቀዝቀዣዎችን፣ የዓሳ ማስገሪያ ጀልባዎችንና ሌሎች የቢሮ መገልገያ ቁሳቁሶችን የቻለውን ዘርፏል፤ ያልቻለውን ደግሞ አውድሟል ብለዋል።

ከዚህም ባሻገር በህብረት ስራ ማህበራቱ ተቀጥረው ሲሰሩ የነበሩ ከ9 ሺህ 700 የሚበልጡት ወገኖች ከስራ ገበታ ውጭ እንዲሆኑ ማድረጉን አስረድተዋል።

በሽብር ቡድኑ የወደሙትንና የተዘረፋትን የህብረት ስራ ማህበራት፣ ዩኒዮኖችና ጽህፈት ቤቶችን ወደ መደበኛ ስራቸው ለመመለስም የደረሰባቸውን የጉዳት መጠን የመለየት ስራ ሲያከናውን መቆየቱን ጠቅሰዋል።

ማህበራቱን ወደ ስራ ለማስገባትም በምዕራብ አማራ የሚገኙ አቅም ያላቸው አቻ ዩኒየኖችና የህብረት ስራ ማህበራት ድጋፍ እንዲያደርጉ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የፌዴራል ህብረት ስራ ኮሚሽንም ድጋፍና እገዛ እንዲያደርግ ጥያቄ ቀርቦ ምላሽ እየተጠበቀ መሆኑን  ተናግረዋል።

በሽብር ቡድኑ ከፍተኛ ውድመት የደረሰባቸውንና ዘረፋ የተፈጸመባቸውን የህብረት ስራ ማህበራት፣ ዩኒየኖችና ጽህፈት ቤቶችን ወደ ቀደመ ስራቸው ለመመለስ 30 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ እንደሚያስፈልግም አብራርተዋል።

መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ክልሎች የህብረት ስራ ማህበራቱን መልሶ ለማቋቋም እየተደረገ ላለው ጥረት ስኬት አስፈላጊውን  ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

”የአርሶ አደሩ ሀብት በሆኑት ህብረት ስራ ማህበራት ላይ አሸባሪ ቡድኑ የከፋ ዘረፋና ውድመት አድርሷል” ያሉት ደግሞ በደሴ ከተማ የሚገኘው የእሪኩም የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበራት ዩኒዬን ተወካይ  አቶ መሳይ አለምነው ናቸው።

በዩኒዬኑ መጋዘን የነበረ ግምቱ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ 8ሺህ 200 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ፣ 260 ኩንታል ስኳርና ሌሎች ንብረቶችን በሽብር ቡድኑ መወሰዳቸውንና መውደማቸውን ገልጸዋል።

ከዩኒዬኑ 105 አባል ማህበራት መካከልም በ101ዱ ማህበራት መጋዘን ውስጥ የነበሩ የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችና የተለያየ ሸቀጣ ሸቀጥ በሽብር ቡድኑ  መዘረፋቸውንም አስረድተዋል።

ዩኒየኑ 20ዎቹን መሰረታዊ የህብረት ስራ ማህበራት በአሁኑ ወቅት ወደ ሰብል ምርት ግብይት ለማስገባት እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቀዋል።

በክልሉ ከ4 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ አባላት ያሏቸው 71 የህብረት ስራ ማህበራት ዩኒየኖችና 25 ሺህ 626 መሰረታዊ የህብረት ስራ ማህበራት እንደሚገኙም ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።