የከተሞችን ፕላን በመጣስ የሚደረግ ማንኛውም ግንባታ እንዲቆም የምክር ቤቱ አሳሰበ

304

ጥር 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) የከተሞችን ፕላን በመጣስ የሚደረግ ማንኛውም ጊዜያዊና ቋሚ ግንባታ እንዲቆም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጭ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

ቋሚ ኮሚቴው የፌደራል ዋና ኦዲተር የ2012/13 የከተማ ፕላን ዝግጅትና አተገባበር ኦዲት ሪፖርትን መሰረት አድርጎ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች ፕላንን በመጣስ የሚካሄዱ ግንባታዎችን አስመልክቶ ጥያቄዎችን አንስቷል።

ለጥያቄዎቹ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የስራ ሃላፊዎች ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን የመሬት ሃብትን በትክክል ለክቶና ቆጥሮ ማስቀመጥ የሚችል ካዳስተር አለመሰራቱ ዋና ምክንያት መሆኑን አብራርተዋል።

በመሆኑም በከተሞች የሚካሄዱ በርካታ ግንባታዎች የተሰራላቸውን ፕላን በመተው እየተከናወኑ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በከተሞች በአንዳንድ የመንግስት ባለስልጣናት ውሳኔ የሚሰሩ ፕላን ያልጠበቁ በርካታ ቋሚና ጊዜያዊ ግንባታዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

እንዲህ አይነቱ ግንባታ "ለኪራይ ሰብሳቢነትና ለመሬት ወረራ በር ከፋች ነው" ሲሉም አስረድተዋል።

በተለያዩ ከተሞች የግንባታ ፕላኑ ከሚፈቅደው አገልገሎት ውጭ በሆነ አሰራር በስራ ፈጠራና በሌሎች ምክንያቶች ለሌላ አገልግሎት የዋሉ እንዳሉ መረጃው አለን በማለት የቋሚ ኮሚቴው አባላት አንስተዋል።

የመንግስት ወጭ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ክርስቲያን ታደለ፤ ችግሩ በተለያዩ ከተሞች በስፋት እየተስተዋለ መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም የከተሞችን ፕላን በመጣስ የሚከናወን ማንኛውም ጊዚያዊና ቋሚ ግንባታ ሊቆም ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር እስከ ጥር 26 ቀን 2014 ዓ.ም በኦዲት ግኝቱ ላይ የታዩትን ጉድለቶች ለመፍታት የሚያስችል የድርጊት መርሃ ግብር እንዲያቀርብ መመሪያ ተሰጥቷል።

የኦዲት ግኝቱን መሰረት በማድረግ ምርመራ እንዲደረግ፣ ተጠያቂነት ያለበት አሰራር እንዲረጋገጥና ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።

በቋሚ ኮሚቴው የተሰጠው መመሪያ መፈፀም አለመፈፀሙን እንዲከታተሉም ለባለ ድርሻ አካላት መመሪያ ተሰጥቷል።

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ዴኤታ ፋንታ ደጀን፤ በከተሞች የሚስተዋለውን ከፕላን ያፈነገጠ ግንባታ ለማስቆም ከክልሎችና ከተማ አስተዳደር ሃላፊዎች ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።

የኦዲት ግኝቱ ላይ ያሉትን ክፍተቶች ለማረም እንደሚሰራ አረጋግጠው ለስኬቱ ቋሚ ኮሚቴውን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። 

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም