የኢትዮጵያና የጂቡቲ የፖሊስ ተቋማት በትብብር በመስራት ብዙ እርምጃ ተጉዘናል

73

ጥር 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) “የኢትዮጵያና የጂቡቲ የፖሊስ ተቋማት በትብብር በመስራት ብዙ እርምጃ ተጉዘናል” ሲሉ የኢትጵጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ገለጹ።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከዚህ ቀደም ከጅቡቲ ብሄራዊ ፖሊስ ኃይል ጋር በድንበር ደህንነት፣ ሽብርተኝነትን በጋራ ለመከላከል፣ በአቅም ግንባታ እና በመረጃ ልውውጥ አብሮ ለመስራት ለፈረመው ሰነድ ተግባራዊነት ቁርጠኛ መሆኑንም አረጋግጧል።

ኮሚሽነር ጄነራሉ የጅቡቲ ብሄራዊ ፖሊስ ኃይል ዋና ዳይሬክተር ኮሎኔል አብዱላሂ አብዲ ፋራህን ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት እንደገለጹት፤ ከመግባቢያ ሰነዱ መፈረም በኋላ ሁለቱ የፖሊስ ተቋማት በትብብር በመስራት ብዙ እርምጃ ተጉዘዋል።

በተለይም መረጃን እና ተፈላጊ ወንጀለኞችን በመለዋወጥ፣ የኢትዮ ጅቡቲ የገቢና ወጪ ትራንስፖርት መተላለፊያዎችን ደህንነት በመጠበቅ እና የፖሊስ መኮንኖችን አቅም በመገንባት በስፋት ሰርተዋል።

ህወሃትን መሰል የሽብር ቡድኖች የሚፈጥሩት የደህንነት ስጋት በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት ላይ ተፅእኖ እንዳለው ገልጸው፤ የሽብር ቡድኖች ከምንም ጊዜውም በላቀ ሁኔታ በመቀናጀት አካባቢያችን እንዳይረጋጋ የሚያደርጉት እንቅስቃሴና የተደራጁ ድንበር ዘለል ወንጀሎች ትኩረታችንን የሚሹ ጉዳዮች ናቸው ብለዋል።

የጅቡቲ ብሄራዊ ፖሊስ ኃይል ዳይሬክተር ኮሎኔል አብዱላሂ አብዲ ፋራህ በበኩላቸው የሁለቱም ሀገራት ፖሊስ ተቋማት ፍላጎታቸው ሰላምን ማረጋገጥ መሆኑን ጠቁመዋል።

“የጀመርነውን መልካም ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የተፈራረምነውን የመግባቢያ ሰነድ ወደ ፈፃሚ አካላት በማውረድ በእኛ በኩልም ለተግባራዊነቱ እንተጋለን” ብለዋል፡፡

በፌደራል ደረጃ ያለው የተጠናከረ ግንኙነት ሀገራቱ ከሚዋሰኑት ከክልል ፖሊስ ኮሚሽነሮች ጋር ተመሳሳይ ግንኙነት ለመፍጠር እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በመድረኩ በኢትዮጵያ የጂቡቲ አምባሳደር አብዲ መሀሙድ፣ የጅቡቲ ኢሚግሬሽን ኃላፊ ኡስማን አህመድ፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሎች፣ የድሬዳዋ፣ የሱማሌና የአፋር  ክልል ፖሊስ ኮሚሽነሮች መገኘታቸውን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ለኢዜአ የላከው መረጃ አመልክቷል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም