የውጭ ጣልቃ ገብነትን ለመከላከል ከኢኮኖሚ ጥገኝነት መላቀቅ ይገባል

63

ጥር 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) የውጭ አገራት ጣልቃ ገብነትን ለመከላከል ከኢኮኖሚ ጥገኝነትን መላቀቅ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለፁ።

ዩኒቨርሲቲው በኢትዮጵያ ጉዳዮች የምዕራባዊያን ጣልቃ ገብነት እና በድህረ ግጭት ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት ከምሁራኑ ጋር አካሂዷል።

በውይይቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ኢትዮጵያ በውጫዊና ውስጣዊ ጫና ስትናወጥ የመጀመሪያዋ አለመሆኑን ጠቅሰዋል።

አገሪቷ ላለፉት ሶስት ሺሀ ዓመታት ያልተሻገረችው የመከራ አይነት የለም ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ የማንንም ነፃነት የማትጋፋውና የራሷንም የማታስደፍረው ኢትዮጵያ በልጆቿ መስዋዕትነት ዛሬም ዳር ድንበሯን አስከብራ ቀጥላለች ብለዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም እንደ አንድ ከፍተኛና አንጋፋ ተቋም በአገራዊ ፈተና ወቅት የራሱን አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በውይይቱ ላይ የታደሙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ ኢትዮጵያ በየጊዜው የሚገጥሟትን ፈተናዎች እያሸነፈች የመጣች ጠንካራና ኩሩ፣ ለነፃነታቸውና ለሉዓላዊነታቸው የማይተኙ ጀግኖች ሕዝቦች ያሏት አገር መሆኗን ጠቅሰዋል።

ሕዝቦቿ አሁንም ፈተና በገጠማት ጊዜ ጥንካሬያቸውን በአንድነት አሳይተዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የገጠማትን ፈተና አሸንፎ ለመውጣት የወደመውን መልሶ በመገንባትና የስነ-ልቦና ጉዳቱንም ለመጠገን የምሁራን ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

አወያዮቹ ፕሮፌሰር ካሳሁን ብርሃኑ፣ ዶክተር ጌታቸው አሰፋ እና ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ፤ የምዕራባዊያን ጣልቃ ገብነትን በተመለከተ የውይይት መነሻ ሃሳቦችን አቅርበዋል።

የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪና መምህረ ፕሮፌሰር ካሳሁን ብርሃኑ፤ ከውጭ ሃይሎች ጋር በአንዳንድ የሚያስማሙ ጉዳዮች ላይ መመካከር ቢቻልም የጣልቃ ገብነት ዝንባሌን ግን በጽናት መታገል ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የውጭ ጣልቃ ገብነትን በጽናት በመታገል አሁን ያለችበት ደረጃ መድረሷን የገለፁት ፕሮፌሰሩ፤ ብሔራዊ ነፃነትና ሉዓላዊነት 'የማይታለፍ ቀይ መስመር ነው' ሲሉ ገልጸዋል።

የሕግ መምህሩ ዶክተር ጌታቸው አሰፋ በበኩላቸው ሚዛኑን በጠበቀ መልኩ ከአገራት ጋር በትብብር መስራት እንደሚገባ አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ሚዛኑን የጠበቀ ዲፕሎማሲ አጋጥሟት የነበረውን ፈተና እንድታልፍ ምክንያት መሆኑን አስረድተው ይህ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ ደግሞ የውጭ ጣልቃ ገብነትን ለመከላከል ከኢኮኖሚ ጥገኝነትን መላቀቅ ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም