የአሸንዳ በዓልን ምክንያት በማድረግ በአክሱም ከተማ የፓናል ውይይት ተካሄደ

80
አክሱም ነሀሴ 24/2010 በትግራይ ማዕከላዊ ዞን ያሉ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ቅርሶችን በምርምርና ጥናት በማስደገፍ ለቱሪዝም ልማት እንዲውሉ እየሰራ መሆኑን የአክሱም ዩኒቨርስቲ አስታወቀ። በዞኑ በየአመቱ ከነሐሴ 24 ጀምሮ ለሦስት ቀናት የሚከበረውን የአይኒ ዋሪ /አሸንዳ/ በዓልን ምክንያት በማድረግ በአክሱም ከተማ ትናንት የፓናል ውይይት ተካሂዷል። በውይይቱ ላይ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት የዩኒቨርሲቲው መምህር መዝገበ ገብረ ሚካኤል  እንዳሉት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ህብረተሰቡን መሰረት ያደረገ ችግር ፈቺ ምርምር በማካሄድ የማልማት ማህበራዊ ኃላፊነት አላቸው። የአክሱም ዩኒቨርሲቲም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በአክሱምና አካባቢው ያሉ ጥንታዊ ቅርሶችን በማልማት የቱሪስት ፍሰት እንዲጨምር ለማድረግ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል። የአክሱም ስልጣኔ የኢትዮጵያና አፍሪካ ብሎም የአለም የስልጣኔ መነሻ እንደመሆኑ መጠን ገና ብዙ ያልተዳሰሱና ያልተጠኑ ጥንታዊ ታሪኮችና ቅርሶች እንዳሉት አስታውሰዋል። እስካሁን ድረስ ያልተዳሰሱና ያልተጠኑ  ጥንታዊ የቅርስ ሃብቶች ለማጥናት ዩኒቨርስቲው አጠናክሮ እንደሚሰራ መምህር መዝገበ ተናግረዋል። ''አክሱም ውስጥ ያሉ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን ለአለም ህዝብ በማስተዋወቅ የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ ኃላፊነቱ ይወጣል'' ብለዋል። ''ባህላዊና ሃይማኖታዊ በዓላት ለቱሪዝም እድገት ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ የቱሪስት ፍሰት እንዲጨምርና ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ዩኒቨርሲቲው በሳይንሳዊ መንገድ ዘርፉን ለማልማትና ለማስተዋወቅ ጥረት ጀምሯል'' ብለዋል። አይኒ ዋሪ/አሸንዳ/ ያለውን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የጎላ  እንደሆነ የገለፁት መምህር መዝገበ ፣ መቻቻልን፣ ሰላምና አንድነትን በማምጣት በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልፀዋል፡፡ በሀገሪቱ የሚከበሩ ሃይማኖታዊና ባህላዊ በአላትን በድምቀት ከማክበር ባለፈ የቱሪዝም ገቢ ምንጭ እንዲሆን  ትልቅ ስራ መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ በአክሱም እና አከባቢው ያለ ጥንታዊ ቅርሶች በማልማትና በማስተዋወቅ ለቱርዝም እድገት እንዲውሉ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ የጀመረውን ሰራ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የገለፁት ደግሞ  የአክሱም ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገብረመድህን ፍሳሃጽዮን ናቸው። ከሦስት ሺህ አመት በፊት ጀምሮ ሲከበር የቆየውን የዓይኒ ዋሪ በዓል የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት/ዩኔስኮ/ ለማስመዝገብ ዝግጅት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ የውይይቱ ተሳታፊ የሆኑትና የአክሱም ከተማ ነዋሪ መምህር ሓጎስ ዘሪሁን በሰጡት አስተያየት ''በሀገሪቱ ያሉትን እምቅ ሃብቶች በተለይ ባህልና ታሪክን ሳይሸራረፍ ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ የሁሉም ህብረተሰብ ድርሻ ከፍተኛ ነው'' ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም