ሁለተኛው የኢጋድ የውሃ ጉዳይ ምክክር መድረክ በኢንቴቤ እየተካሄደ ነው

94

ጥር 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) ሁለተኛው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የውሃ ጉዳይ የምክክር መድረክ በኡጋንዳ ኢንቴቤ እየተካሄደ ይገኛል።

"የከርሰ ምድር ውሃ ድርቅን ለመቋቋም" በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ በሚገኘው በዚህ የምክክር መድረክ የቀጣናው የውሃ አቅርቦትና የድርቅ ሁኔታ ላይ እየተመከረ ነው።

የመድረኩ ዋና ዓላማ የከርሰ ምድር ውሃ ለአየር ንብረት ለውጥ እና ድርቅ መቋቋም፣ ለሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት የሚኖረው ፋይዳ ላይ በስፋት መምከር መሆኑ ተጠቁሟል።

ከዚህ በተጨማሪም የከርሰ ምድር ውሃ አጠቃቀም አቅም ግንባታ፣  የከርሰ ምድር ውሃ ፋይናንስ እና የቴክኖሎጂ ልማት ፈጠራ ሰፊ ምክክር የሚደረግባቸው ርእሰ ጉዳዮች መሆናቸው ተገልጿል።

የኢጋድ አባል ሀገራት የውሃ ዘርፍ አመራሮች፣ የግሉ ዘርፍ እና የልማት አጋሮች የከርሰ ምድር ውሃ ለቀጣናው ዘላቂ ልማት ስላለው ሚና እንዲወያዩ እድል የፈጠረ መድረክ ስለመሆኑም ተነግሯል።

ከውሃ ጋር በተያያዘ የታቀዱ ፕሮጀክቶች እና ፕሮግራሞችን በትብብር ለመስራት እድል ይፈጥራል ተብሏል።

ፖሊሲ አውጪዎች፣ የቴክኒክ ባለሙያዎች፣ የግሉ ሴክተር ተዋናዮች እንዲሁም የሲቪል  ድርጅቶች ከኢጋድ አጠቃላይ ስትራቴጂ ጋር በተጣጣመ  መልኩ ለከርሰ ምድር ውሃ ልማት የበኩላቸውን አስተዋፅዖ የሚያደርጉበትን መንገድ በማመላከት ረገድም ምክክሩ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ነው የተገለፀው።

የምክክር መድረኩ  በከርሰ ምድር ውሃ ልማትና አስተዳደር የኢንቨስትመንት እድሎችን ሊያመጣና  አዳዲስ ፈጠራዎችን ሊያመላክት እንደሚችልም ተጠቁሟል።

መድረኩ በፓናል ውይይቶች፣ በጥናትና ምርምር ውጤቶች እና በሙያዊ ገለጻዎችን እያስተናገደ እስከ ጥር 19 ቀን 2014 ዓ.ም ይቀጥላል።

አንደኛው የኢጋድ የውሃ ውይይት መድረክ በኬንያ ናይሮቢ መካሄዱ ይታወሳል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም