አገራዊ ምክክሩ የተረጋጋችና ችግሮቿን በውይይት ብቻ የምትፈታ አገር ለመገንባት መሰረት የሚጥል ነው

96

ጥር 17/2014/ኢዜአ/ አገራዊ ምክክሩ የተረጋጋችና ችግሮቿን በውይይት ብቻ የምትፈታ አገር ለመገንባት መሰረት የሚጥል መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የሲቪክ ማሕበራት ገለጹ።

ማሕበራቱ እንደሚሉት፤አገራዊ ምክክሩ በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ስርዓት እያደገ እንዲሔድ የላቀ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

በህዝቦች መካከል መቀራርብን በመፍጠር የተረጋጋች አገር ለመገንባት ሚናው የጎላ መሆኑንም እንዲሁ፡፡

የአዲስ አበባ ሴቶች ማሕበር ሊቀመንበር ወይዘሮ ሁሉአገርሽ ታዘዘ፤ አገራዊ ምክክሩ በየቦታው የሚታዩት ሁለንተናዊ ችግሮችን በመፍታት ረገድ አይነተኛ መፍትሔ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

በኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት ሲንከባለሉ የቆዩ ችግሮች መኖራቸውን አስታውስው፤ ከዚህ አኳያ አገራዊ ምክክሩ እነዚህ ችግሮችን በመፍታት ረገድ ከፍተኛ አበርክቶ እንደሚኖረውም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የተጀመረውን ለውጥ ተከትሎ ለረዥም ዘመናት ስር የሰደዱ አገራዊ ችግሮችን ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ መቆየቱንም ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም አገራዊ ምክክሩ እነዚህ ጥረቶችን ውጤታማ ለማድረግ ጉልህ ሚና እንደሚኖረውም ነው የገለጹት፡፡

የኢትዮጵያ መምህራን ማሕበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ዮሐንስ በንቲ በበኩላቸው ማሕበሩ ቆየት ያሉና በየጊዜው እየተንከባለሉ የመጡ ችግሮችን በውይይትና ምክክር መፍታት ተገቢ ነው ብሎ ያምናል ብለዋል፡፡

በመሆኑም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ መሆን እንዳለባቸውም ነው ያነሱት፡፡

አገራዊ ምክክሩ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ባሻገር በየደረጃው ያሉ ሁሉንም የኀብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ያደረገ ሊሆን እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

ሁሉም ዜጋ ችግሮችን በውይይትና ምክክር በመፍታት የተረጋጋች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ የማሸጋገር ኃላፊነት እንዳለበትም ዶክተር ዮሐንስ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኢትዮጵያ በተለያዩ  ጉዳዮች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በምክክርና በውይይት ለመፍታት እንዲቻል አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 እንዲቋቋም ማድረጉ ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም