ለሙት አመት ዝክር የተዘጋጀ 100ሺህ ብር ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ ተበረከተ

99

አፋር ጥር 17/2014 (ኢዜአ) ለሙት አመት መታሰቢያ ዝክር የተዘጋጀ 100 ሺህ ብር በአፋር ክልል በአሸባሪው ህወሃት ጥቃት ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ ተበረከተ።

በአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑ  ወይዘሮ ፈንታየ ብርሃኔ ለባለቤታቸው ኢንጂነር ገብረየስ ሃይሌ 3ኛ ሙት አመት መታሰቢያ ለመዘከር ያሰቡትን 100 ሺህ ብር በአሸባሪው ህወሀት ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ እንዲውል ዛሬ አበርክተዋል ።

በጎ አድራጊዋ በዚህ ወቅት እንዳሉት ባለቤታቸው በአፋር ክልል ከወጣትነት  እድሜያቸው ጀምሮ እስከ ጉልምስናቸው ከመንግስት ሰራተኛነት እስከ አገር በቀል የልማት አጋር ድርጅት እስከማቋቋም  ለህብረተሰቡ ኑሮ መሻሻል ሰርተዋል።

ባለቤታቸው  "ድጋፍ ለዘላቂ ልማት" የተባለ አገር በቀል ግብረ-ሰናይ ድርጅት አቋቁመው በክልሉ የተለያዩ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም በመስኖ የታገዘ የግብርና ስራ እንዲስፋፋ በሰሩት ተግባር በክልሉ መንግስትና በአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ ዘንድ በስፋት ይታወቁ እንደነበር አስታውሰዋል።

ኢንጂነሩ  ህይወታቸው ከማለፉ በፊት በክልሉ ጀምረዋቸው የነበሩ የልማት ስራዎችን ለማስቀጠል  ቤተሰቦቻቸው ዝግጁ መሆናቸውን  ወይዘሮ ፋንታየ አስታውቀዋል።

በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት  የቀድሞው የክልሉ አርብቶ አደርና ግብርና ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ አወል ሜኤ በበኩላቸው  ኢንጂነር ገብረየስ በቀድሞ ተንዳሆ እርሻ ልማት ውስጥ ከጀማሪ ኢንጂነርነት ጀምሮ በተለያዩ የስራ መስኮች ለአፋር ህዝብ በጎ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

በተለይም ባለፉት 20 አመታት ውስጥ ባቋቋሙት ግብረሰናይ ድርጅት በክልሉ ከ10 በላይ ወረዳዎች  የመስኖ መሰረተ-ልማቶችን በማስፋፋትና ዘመናዊ ግብርናን በማስተዋወቅ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ጠቅሰዋል።


ድጋፉን የተረከቡት የክልሉ ፍይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ሃላፊና ክልላዊ የሃብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አህመድ መሀመድ  የኢንጂነር ገብረየስ ቤተሰቦች ከሚኖሩበት አዲስ አበባ ከተማ አፋር በመምጣት  አጋርነታቸውን በመግለጻቸው ምስጋና አቅርበዋል።


በሽብር ቡድኑ ጥቃት ያጋጠመን የዜጎች መፈናቀልና የንብረት ውድመት መቋቋም የሚቻለው በሁሉን-አቀፍ የህብረተሰብ ድጋፍ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም