ሀገራዊ ምክክሩ በኢትዮጵያ ስር የሰደዱ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ጉልህ ሚና ይኖረዋል

183

ጥር 17/2014/ኢዜአ/ ሀገራዊ ምክክሩ በኢትዮጵያ ስር የሰደዱ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ጉልህ ሚና እንደሚኖረው አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ ተናገረ።


አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ ኢትዮጵያ በቅርቡ እንደምታካሂደው በሚጠበቀው ሀገራዊ ምክክር አስፈላጊነት ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርጓል።

በመንግሥት የተቋቋመው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን እንደ ሀገር መግባባት ያልተደረሰባቸው ሀገራዊ ትላልቅ ጉዳዮች ላይ እልባት በመስጠት ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ነው አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ የተናገረው።

ምክክሩ የተለያዩ አለመግባባቶች እንዲከስሙና በሂደትም ለሀገርና ለህዝብ ጠቃሚ የሆኑ አጀንዳዎች የሚወጡበት መሆኑንም ነው ያስረዳው።

ሠላም፣ ዴሞክራሲና ፍትህ የሚፈልግ አካል መነጋገርና መመካከር አለበት ያለው አርቲስት ደበበ እሸቱ የሀገራዊ ምክክሩ የሚያመጣውን ጠቀሜታ መረዳት ይገባልም ነው ያለው።

ሀገራዊ ምክክሩ በኢትዮጵያ እየተደራረቡ የመጡ የቆዩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት አይነተኛ መፈትሄ መሆኑንም ተናግሯል።

በሀገራዊ ምክክሩ የሚሳተፉ አካላት ቅንነትን ተላብሰውና ሀገርን አስቀድመው በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና መግባባት ለመፍጠር ዝግጁ ሆነው መቅረብ ይኖርባቸዋል ብሏል።

ምክክሩ ለሀገር ሰላምና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ትልቅ አበርክቶ እንዳለው ግንዛቤ በመውሰድም ተሳታፊ አካላት ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ይጠበቃል ብሏል።

መንግሥት በኢትዮጵያ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ያቋቋመው ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ለሰላም ያላቸውን ቁርጠኝነት ለዓለም ያሳያል ብለዋል።

የውጭ ሃይሎችን ያልተገባ ፍላጎት የሚያከሽፍና የኢትዮጵያን ገጽታ በአዎንታዊ መልኩ ለመቀየርም ድርሻው ትልቅ መሆኑን አርቲስት ደበበ እሸቱ ጠቅሷል።

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች በመሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ልዩነት በምክክር ለማስተካከል ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 መቋቋሙ ይታወሳል።

ኮሚሽኑም መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አካታች ሀገራዊ ምክክሮችን በማካሄድ የተሻለ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ይሰራል።

በአዋጁ አንቀጽ 12 ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት ሀገራዊ ምክክሮች ተቀባይነትና ተዓማኒነት እንዲኖራቸው ተቋሙን በገለልተኝነት የሚመሩ 11 የዕጩ ኮሚሽነሮች ጥቆማም ከህዝቡ፣ ከፖለቲካ ድርጅቶችና ከሲቪል ማኅበራት ጥቆማ ተካሂዶ ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም