የደቡብ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በዳሰነች ወረዳ በጎርፍ አደጋ ለችግር የተጋለጡ አካባቢዎችን እየጎበኙ ነው

91

ጂንካ፤ ጥር 17/2014 (ኢዜአ) የደቡብ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ልዑካን ቡድን በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ በጎርፍ አደጋ ለችግር የተጋለጡ አካባቢዎች እየጎበኙ ነው።

የዳሰነች ወረዳ አስተዳደር ተወካይ አቶ ቹመሬ የራ ለልዑካን ቡድኑ እንደገለጹት ከወራት በፊት በአካባቢው በተከሰተው የጎርፍ አደጋ 45 ሺህ የሚሆኑ አርብቶ አደሮችን ከመኖሪያ ቀያቸው አፈናቅሏል።

በአደጋው በወረዳው የሚገኙ የጤናና የትምህርት ተቋማት ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን አመልክተዋል።

ከ98 ሺ ሄክታር በላይ የሚሆን የግጦሽ መሬት በውሃ ሙላት መጥለቅለቁን ያስታወሱት አስተዳዳሪው፤ 2 ሚሊዮን የሚሆኑ የቀንድ ከብቶች ለመኖ እጥረት መጋለጣቸውን አስረድተዋል።

በአደጋው ምክንያት ከመኖሪያ ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የተለያዩ ድጋፎች እየተደረጉ መሆኑን ያስረዱት አቶ ቹመሬ ከአደጋው ስፋትና ከተጎጂዎች ቁጥር መብዛት አንፃር ድጋፍ በቂ አለመሆኑን አመልክተዋል።

የልዑካን ቡድኑ አባላት በአካባቢው በሚኖራቸው ቆይታ አደጋውን በዘላቂነት መቅረፍ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከአርብቶ አደሩ ማህብረሰብ ተወካዮችና ከወረዳው አመራር አካላት ጋር ይመክሯሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የልዑካን ቡድኑ በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ የተመራ መሆኑ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም