ሀሰተኛ መታወቂያ ለጠላት አሳልፈው ለመስጠት ሲንቀሳቀሱ የተደረሰባቸው ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

127

ጎንደር ፣ ጥር 17/2014 (ኢዜአ ) በጎንደር ከተማና ዙሪያ ወረዳ 314 ሀሰተኛ የቀበሌ መታወቂያ ለጠላት አሳልፈው ለመስጠት በድብቅ ሲያጓጉዙ የተገኙ ሁለት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የጎንደር ከተማ ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት ዋና ክፍል ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር እየሩስ አስማረ ለኢዜአ እንደገለጹት ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አንዱ ጥር 13 ቀን 2014 ዓም በተደረገ ክትትል በጎንደር ዙሪያ ወረዳ እንፍራዝ ከተማ 104 ሀሰተኛ መታወቂያዎችን ይዞ ተገኝቷል።

ሌላው ተጠርጣሪ ግለሰብም  ጥር 14 ቀን 2014 ዓም በጎንደር ከተማ አዘዞ በሚገኘው መናኽሪያ አካባቢ 210 ሀሰተኛ መታወቂዎችን ይዞ መገኘቱን ተናግረዋል።

ከህብረተሰቡ የደረሰን  ጥቆማ መሰረት በማድረግ በፀጥታ ሃይሉ በተደረገ ጥብቅ የደህንነት ክትትል ግለሰቦቹ ከነ ሀሰተኛ መታወቂያው እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን አስታውቀዋል።

በአጠቃላይ  314 ሀሰተኛ መታወቂያዎች በግለሰቦቹ እጅ መያዛቸውን አብራርተዋል።

ሀሰተኛ መታወቂያዎቹ በምእራብ ጎንደር ዞን በመተማ ወረዳ ሽኩራ በተባለ ቀበሌ ስም የተዘጋጁና ለጠላት ሃይሎች እንዲደርሱ ለማድረግ ታስቦ የነበረ መሆኑን ዋና ኢንስፔክተሯ ተናግረዋል፡፡

ተጠርጣሪ ግለሰቦቹ በህግ ጥላ ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ጠቁመው ሀሰተኛ መታወቂያዎቹ በባህር ዳር ከተማ በህገ-ወጥ መንገድ የታተሙ ስለ መሆናቸው መረጃዎች እንደሚያመለክቱ ገልጸዋል፡፡

"የሀሰተኛ መታወቂያዎች ስርጭትና ህትመት የሀገርን ሰላምና የህዝብን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ወንጀል ነው" ብለዋል፡፡

መታወቂያዎቹ ለሽብር ቡድኖች የጥፋት ተልእኮ ማስፈጸሚያ ሊውሉ የሚችሉ በመሆናቸው ህዝቡ ከፖሊስና ከፀጥታ አካላት ጋር የጀመረውን ወንጀልን የመከላከል  ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም