ከአንበሳ መንጋ ጋር ለመፋጠጥ የዳረገ ድርቅ

1784

የስድስት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ ኦሶብ ሀዛን ድርቅ ያስከተለው ርሀብ ከአንበሳ መንጋ ጋር እስከመፋጠጥ ያደረሰ ፈተና እንዲጋፈጡ አስገድዷቸዋል።

ኦሶብ ሀዛን በሶማሌ ክልል አፍዴር ዞን ሐርጌሌ ወረዳ ነዋሪ ናቸው።

የኢዜአ ሪፖርተር በአካባቢው የድርቁ ተጎጂዎችን ለማናገር በተገኘበት አጋጣሚ የችምባ ቀበሌ ነዋሪዋ ኦሶብ በድርቁ ሰበብ በጣረ-ሞት ላይ ካለች ፍየላቸው ጎን ቁጭ ብለው እየተከዙና እያለቀሱ ነበር ያገኛቸው።

ወራትን ያስቆጠረው ድርቅ ከወይዘሮ ኦሶብ 20 ከብቶች 19ኙን ቀጥፏል።

አሁንም ፍየሎቻቸው ከጎናቸው ቆመው ሲሞቱ እየተመለከቱ ነው።

‘በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ’ እንዲሉ ከሀዘናቸውና ለቅሷቸው ሳይፅናኑ ርሀብና ጥማትን ለማስታገስ ሲጥሩም ለአካል ጉዳትም ተዳርገዋል።

ለዚህ መነሻውም የአንበሳ መንጋ መንጋጋ ሲሳይ ላለመሆን ያደረጉት ግብግብ ውጤት ነው።

ነገረ ታሪኩንም እንዲህ ይተርኩታል።

አርብቶ አደሯ ከ20 ከብቶቻቸው መካከል በድርቅ ሳይሞት የተረፈላቸውን ብቸኛ በሬ ውሃ ለማጠጣትም ሆነ ለራሳቸው ለመጠጣት እንደማንኛውም የአካባቢው ሰው በቀንና በጨለማ ውሃ ፍለጋ መንከራተት ነበረባቸው።

በአንድ ዕለት 30 ኪሎ ሜትር በላይ ከሚርቀው የውሃ ምንጭ ለመቅዳት በሌሊት ያመራሉ።

ከድካማቸው በላይ ዕለቱ እንደወትሮው መልካም አልነበረምና፣ ውሃ መቅጃው ስፍራ እንደደረሱ በአንበሳ መንጋ ይወረራሉ።

በሁነቱ የተደናገጡት ባልቴቷ አርብቶ አደር ባሰሙት የድረሱልኝ ጥሪ በአካባቢው የነበሩ ሌሎች ውሃ ቀጂዎች ባሰሙት ድምፅ ተርፈዋል።

ርሀብ ጊዜ አይሰጥምና፤ ድርቅ የወለደው መጠማትና ርሀብ እነወይዘሮ ኦሶብን ከጫካው ንጉስ ከአንበሳ መንጋም ጋር ከመተናነቅ አላዳናቸውም።

እናም የአንበሳ መንጋ ሲሳይ ላለመሆን ሲሮጡ በእጃቸው ላይ ጉዳት ቢደርስም ነፍሳቸውን ግን አትርፈዋል።

በአካባቢው በተከሰተው ድርቅ እንስሳት እያለቁ መሆኑን ገልፀው፤ ርሀብና መጠማቱ ከእንስሳት አልፎ ወደሰዎች ከተሸጋገረ ሰነባብቷል ብለዋል።

30 ኪሎ ሜትር ተመላልሶ ለመጠጣት ደግሞ ልክ በእኔ ላይ እንደደረሰው ጉዳት ሁሉ አስቸጋሪ አድርጎብናል ይላሉ።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼