ኢትዮጵያዊያን ለሀገራቸው ዲፕሎማት ሆነው እንዲቆሙ የሚያስችል አሳታፊ አሰራር መከተል ያስፈልጋል

208

ጥር 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያን ለሀገራቸው ዲፕሎማት ሆነው እንዲቆሙ የሚያስችል አሳታፊ አሰራር መከተል እንደሚያስፈልግ የዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የዩኒቨርሲቲው መምህራን እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ዜጎችን በማሳተፍ እየተካሄደ ያለው የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።

አንዳንድ ምዕራባውያን አገሮችና መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያን እውነት በመሸፈን ሲያደርጉት የነበረውን ያልተገባ ጫና በተለያዩ አገሮች የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆችን በማሳተፍ የተካሄደው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ውጤት ማምጣቱን ገልጸዋል።

በዩኒቨርሲቲው የህዝብ ግንኙነትና የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ አቶ ሙሉዓለም ኃይለማርያም እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገባ ግልጽ መልዕክት በዜጎች በኩል ተላልፏል።

በአገር ውስጥ መንግስት ለዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ያደርግ የነበረው ማብራሪያ ግልጽነት መፍጠሩን ጠቅሰው፤ ሐሰተኛ ዘገባ ላይ የተጠመዱ መገናኛ ብዙሃን እንዲጋለጡ በማድረግ የዜጎች ሚና የጎላ እንደነበር ተናግረዋል።

መንግስትና ህብረተሰቡ በተቀናጀ አግባብ ተፅኖዎችን ለመመከት የሄዱበት ርቀት ለዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ትምህረት የሰጠ መሆኑን አቶ ሙሉዓለም አመልክተዋል።

በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስና ስነ ሰብ ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ኤፍሬም አሀዱ በበኩላቸው ኢትዮጵያዊያን በሁሉም ዘርፎች ሀገር ያላትን ጥንካሬ አስጠብቆ ለማስቀጠል፣ ገፅታዋን ለመገንባትና ከተደቀነባት ፈተና ለመውጣት የዲፕሎማሲ ሂደቱን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

አደጋውን ለመመከት ኢትዮጵያዊያን ለሀገራቸው ዲፕሎማት ሆነው እንዲቆሙ የሚያስችል አሳታፊ አሰራር መከተል ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሀሰት ፕሮፓጋንዳዎችን ለመመከት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በተለይም ተማሪዎችና ምሁራን በተደራጀ አግባብ በዲጂታል ዲፕሎማሲው ዘርፍ ትግል ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።