በአማራ ክልል የማዕድን ሃብትን ጥቅም ላይ ለማዋል እየተሰራ ነው

246

ባህር ዳር፣ ጥር 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ያለውን የማዕድን ሀብት በጥናት በመለየት አልሚ ባለሃብቶችንና ወጣቶችን በስፋት ለማሰማራት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በቋራና ጃዊ ወረዳዎች ያካሄደው የስነ-ምድር ጥናትና የካርታ ሥራ የመጨረሻ ውጤት ግምገማ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ታምራት ደምሴ እንደተናገሩት፤ ክልሉ ያለውን ዕምቅ የማዕድን ሃብት ጥቅም ላይ ለማዋል ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር በተለያዩ ቦታዎች ጥናት እያካሄደ ነው።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲም በ2010 ዓ.ም አጋማሽ የቋራና የጃዊ የስነ-ምድር ጥናትና ካርታ ስራ ለማከናወን የ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ውል ወስዶ የጥናት ስራውን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው ባካሄደው ጥናት የማዕድን አይነቶችን የመለየት፣ ክምችታቸውን የማስላትና የሚገኙበትን ቦታ ለይቶ ካርታ የማዘጋጀት ስራ ማከናወኑን ተናግረዋል።

"በጥናት የተለዩ ማዕድናትን አልምቶ ለኮንስትራክሽን፣ ለፋብሪካዎችና ለግብርና ግብዓት  እንዲያገለግሉ ይሰራል" ብለዋል።

ሃብቱን ለማልማት ባለሃብቶችን በማሳተፍ ለክልሉ የኢኮኖሚ እድገትና ለወጣቱ የሥራ ዕድል ፈጠራ የበኩሉን እንዲወጣ ይደረጋል።

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የስነ-ምድር ጥናት መምህር፣ ተመራማሪና የጥናት ቡድን መሪ ዶክተር ዳዊት ልበኔ በበኩላቸው፣ በቋራና ጃዊ ወረዳዎች ለአራት ዓመታት በተካሄደው ጥናት ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።

"በወረዳዎቹ በ11 ሺህ 458 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት ላይ የብረት፣ የወርቅ፣ የእብነበረድ፣ ሲልካ ሳንድና ሌሎች ማዕድናት ክምችት እንዳሉ ተረጋግጧል" ብለዋል።

እንዲሁም በቀላሉ ሊገኙ የማይችሉ ማዕድናትም በአካባቢው መገኘታቸውን ጠቁመዋል።

"በክልሉ ያለውን ዕምቅ የማዕድን ሃብት ለማልማት ቢሮው የዩኒቨርሲቲዎችን አቅም ለመጠቀም እያደረገ ያለው ጥረት የሚያበረታታ ነው" ያሉት ደግሞ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጂኦሎጂ ትምህርት ክፍል መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ዘላለም ልየው ናቸው።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲም ቀደም ሲል በሰሜን ወሎ ዞን በሚገኙ አምስት ወረዳዎች የኦፓልና ለኮንስትራክሽን መስሪያ የሚያገለግሉ ማዕድንናትን ለመለየት የስነ ምድር ጥናት ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰዋል።

ዩኒቨርሲቲው አሁን ላይ ከቢሮው ጋር ውል ወስዶ ለስሚንቶ መስሪያ የሚሆነውን የላይም ስቶን የክምችት መጠን እያጠና መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም