አርሶ አደሩ ፈጥኖ ወደ መስኖ ልማት መግባቱ የኢኮኖሚ ጫናን ለመቀነስ ፋይዳው የላቀ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አርሶ አደሩ ፈጥኖ ወደ መስኖ ልማት መግባቱ የኢኮኖሚ ጫናን ለመቀነስ ፋይዳው የላቀ ነው

ደብረ ብርሃን፣ ጥር 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) አርሶ አደሩ ከጦርነት ድል ማግስት ፈጥኖ ወደ መስኖ ልማት መግባቱ ሊከሰት የሚችለውን የኢኮኖሚ ጫና ለመቀነስ ፋይዳው የላቀ መሆኑን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ አስታወቁ።
ርዕሰ መስተዳድሩ በሰሜን ሸዋ ዞን በመስኖና በኩታ ገጠም እየለማ ያለ የቆላ ስንዴን በጎበኙበት ወቅት እንዳሉት፤ አርሶ አደሩ በተካሄደው የህልውና ዘመቻ ጠላትን ከመፋለም ጎን ለጎን በመኽር የለማውን ሰብል በመሰብሰብ ድርብ ተጋድሎ አድርጓል።
በአሁኑ ወቅትም በበጋ መስኖ ልማት በስፋት በመሳተፍ እያካሄደ ያለው እንቅስቃሴ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚገበየውን የስንዴ ምርት በማስቀረት ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ እየተካሄደ ያለውን የስንዴ ልማት የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኃይለማርያም ከፍያለው በበኩላቸው በክልሉ በበጋ የመስኖ ስንዴ 80 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ እስካሁን 34 ሺህ ሄክታር መሬት ማልማት መቻሉን ጠቁመዋል።
እቅዱን ለማሳካትም አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለአርሶ አደሩ ሙያዊ እገዛ በመስጠት 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገብረፃድቅ በበኩላቸው የዞኑ አርሶ አደሮች ከጦርነቱ ማግስት ጀምሮ ወደ መደበኛ የልማት ስራ ገብተው እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
እስካሁን በዞኑ 1 ሺህ 300 ሄክታር መሬት በቆላ ስንዴ መልማቱንና በቀጣይም ልማቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።