የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ሳይጠናቀቅ ለነዋሪዎች በማስተላለፍ እየደረሰ ያለው አላስፈላጊ ወጭ ሊታረም ይገባዋል

92

አዲስ አበባ፣  ጥር 16/2014(ኢዜአ)  የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ሳይጠናቀቅ ለነዋሪዎች በማስተላለፍ እየደረሰባቸው ያለው አላስፈላጊ ወጭ በቀጣይ ሊታረም እንደሚገባው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

በጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ የሚስተዋለውን የመሰረተ ልማት አለመሟላት ችግር ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የከተማና የመሰረተ ልማት ሚኒስቴር አስታውቋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ባለፉት ስድስት ወራት በሚኒስቴሩ በዕቅድ ተይዘው ሲከናወኑ የነበሩ ተግባራትን ክንውን ገምግሟል።

የከተማና የመሰረተ ልማት ሚኒስቴር በስድስት ወራት ሲያከናውናቸው የነበሩ በተለይም የጋራ በመኖሪያ ቤቶች ግንባታ፣ የከተሞች መሰረተ ልማት ማስፋፊያ፣ የምግብ ዋስትና፣ በመንግስት ህንፃ ግንባታ፣ የመንገዶች አስተዳደር እና ሌሎች አፈፃጸሞችን አቅርቧል።

የፋይናንስ እጥረት፣ በዘርፉ የተሰማሩ ተቋራጮችና አማካሪዎች በሙሉ አቅምና ፍላጎት አለመስራት፣ የጸጥታ ችግር እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች በዘርፉ ያጋጠሙ ችግሮች መሆናቸው ተነስቷል።

የሚኒስቴሩን አፈፃፀም ሪፖርት የገመገመው ቋሚ ኮሚቴው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ሳይጠናቀቅ ለነዋሪዎች የሚተላለፍ በመሆኑ ለአላስፈላጊ ወጭ እየዳረጋቸው መሆኑን አንስቷል።

በተለይም በአዲስ አበባ የግንባታ ሂደታቸው ሳይጠናቀቅ ለነዋሪዎች የተላለፉ የ20/80 እና የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዜጎችን ለከፍተኛ ውጭ እየዳረጉ በመሆኑ ችግሩ ሊታረም ይገባል ብሏል ቋሚ ኮሚቴው።

ዜጎች የቤት ባለቤት ለመሆን ገንዘብ ቆጥበው ለመንግስት ጥያቄ እያቀረቡ ቢሆንም በስድስት ወራት ግንባታ ለማስጀመር አፈፃጸሙ ዝቅተኛ መሆኑ ታውቆ ቀጣይ ስራ የሚጠይቅ እንደሆነም ተነስቷል።

ዘመናዊ የይዞታ መረጃ ስርዓትን በመዘርጋት ሰነድ አልባ ይዞታዎችንና ህገወጥ የመሬት ወረራን በመከላከል ሌብነትና ብልሹ አሰራርን መቀነስ እንደሚገባ ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።

በጸጥታ ችግር እና በግዥ ሂደት ምክንያት ለመገንባት በዕቅድ ተይዞ ያልተጠናቀቁ የመንግድ ግንባታና ጥገና ስራዎችን ከተያዘው ዕቅድ ጋር በማጣጣም መስራት ይገባል ተብሏል።

የከተማ መሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ፤ በኮንስትራክሽንና መሰረተ ልማት ዘርፉ ላይ ዝቅተኛ አፈፃጸም የተመዘገባባቸውን ግቦች ለማሻሻል በልዩ ትኩረት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የመጨረሻ የግንባታ ምዕራፍ ላይ የሚገኙ ቤቶችን ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ ለቤት ፈላጊዎች በፍጥነት ማስተላለፍ እንደሚገባም እንዲሁ።

የከተማና የመሰረተ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ፤ በቋሚ ኮሚቴው የተሰጡ ግብረ መልሶችን በመውሰድ ለተሻለ ውጤት እንሰራለን ብለዋል።

የከተማና የመሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴዔታ አቶ ሔኖስ ወርቁ፤ ወሳኝ የሆነ የመሰረተ ልማት አቅርቦት የሌላቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች የመልካም አስተዳደር ችግር እንዳይፈጥሩ ከብሔራዊ ባንክ ተጨማሪ በጀት መጠየቁን ገልጸዋል።

ግንባታቸው ሙሉ ለሙሉ ሳይጠናቀቅ ለተጠቃሚ የተላለፉት የ40/60 እና 20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ችግር ዳግም እንዳይከሰት በማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በጉድለት የተነሱ ችግሮችን ለማስቀረት በዘመናዊ የቴክኖሎጂ የተደገፉ የህግ፣ የብቃትና የሙያ የአሰራር ስርዓቶችን በመዘርጋት ለተሻለ ውጤት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም