ኮሚሽኑ በአማራ ክልል በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች እና የፖሊስ ተቋማት የገንዘብና አይነት ድጋፍ አደረገ

164

ጥር 16 ቀን 2014 (ኢዜአ)የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በአማራ ክልል በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች እና የፖሊስ ተቋማት ከ9 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጣ የገንዝብና አይነት ድጋፍ አደረገ፡፡

ድጋፉን የኮሚሽኑ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ኮምቦልቻ በመገኘት አስረክበዋል፡፡

ኮሚሽኑ ለኢዜአ እንደገለጸው፤ “በጀግንነት እንጠብቃለን ህዝባዊ ወገንተኝነታችንን በድጋፋችን እናረጋግጣለን ” በሚል መሪ ሃሳብ ነው ድጋፉን ያደረገው፡፡

በዚህም የ1 ሚሊዮን ብር የገንዘብ እና በአጠቃላይ ከ8 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ የአይነት ድጋፍ አድርጓል፡፡

የአይነት ድጋፉም የምግብ ፍጆታዎች፣አልባሳት፣የቢሮ እቃዎችና ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችን ያካተተ መሆኑንም ነው በኮሚሽኑ የልዩ ጽህፈት ቤት እና ስታፍ ዳይሬክተር ረዳት ኮሚሽነር አህመድላዲን ጀማል የገለጹት፡፡

በአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የሰው ሃብት ልማት ዘርፍ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ሃብታሙ ሲሳይ በበኩላቸው ኮሚሽኑ የክልሉን ህዝብ በማስተባበር የወደሙ የፖሊስ ተቋማትን መልሶ የመገንባት ስራ እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ክልሉን መልሶ ለማደራጀት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቅሰው፤የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በሽብር ቡድኑ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት እና ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ለማቋቋም ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

‼️

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼️

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼️

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼️