አዲሱ የንግድ ህግ ፍትሐዊ አሰራርን በመዘርጋት ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ፋይዳው የጎላ ነው

177

አዲስ አበባ፣ ጥር 16/2014 (ኢዜአ) አዲሱ የንግድ ህግ ፍትሐዊ የአሰራር ስርዓትን በመዘርጋት ለአገር ኢኮኖሚ እድገት ፋይዳው የጎላ መሆኑን የፍትሕ ሚኒስቴር አስታወቀ።


ህጉ በሚያዚያ ወር 2013 ዓም ጸድቆ ተግባራዊ እየተደረገ ሲሆን፤ የፍትህ ሚኒስቴር ህጉን የማስተዋወቅ ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጿል።

ሚኒስቴሩ በዛሬው እለት የዚሁ ስራ አካል የሆነ የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ አካሄዷል፡፡

የሚኒስቴሩ የሕግ ጥናት ማርቀቅና ማጠቃለል ዳይሬክተር አቶ በላይሁን ይርጋ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ከ50 ዓመታት በላይ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው የንግድ ህግ ተሻሽሎ በአዲስ እንዲተካ ተደርጓል።

ለዚህም ምክንያቱ ነባሩ የንግድ ህግ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ በዘርፉ ያለውን ውድድር ያላገናዘበ ስለነበር ነው ብለዋል፡፡

አዲሱ ሕግ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና የዘርፉን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ሰፊ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አንስተዋል።

በዘርፉ በርካታ ለውጦቶችን ይዞ መምጣቱንና ግለሰቦችን፣ ማህበሮችንና ድርጅቶችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በማሕበራት መደራጀትና መዋሐድን ጨምሮ በሀገሪቱ ያሉ የባንክና ኢንሹራንስ አሰራር ከዓለም አቀፍ ተቋማት አንፃር እንዲቃኝ ማደረጉንም ነው ያመለከቱት።

በመሆኑም ተቋማት አዲሱን የንግድ ሕግ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ አሰራሮችን በአግባቡ እንዲዘረጉ ለማድረግ ሕጉን የማስተዋወቅ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ያዛቸው በለው በበኩላቸው የተሻሻለው ሕግ የዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።

ሕጉ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እንደሚያግዝና በዚሁ እድል ተጠቃሚ ከሚሆኑ አካላት ልምዶችን ለመቅሰም እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ነባሩ የንግድ ሕግ 5 ጥራዞች የነበሩት ሲሆን አዲሱ ሕግ ወደ ሦስት ጥራዞች ዝቅ እንዲል ተደርጓል።