ወጣቶች ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ሚናቸው ከፍተኛ ነው

80

ጥር 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) ወጣቶች ኢትዮጵያ በቅርብ ለምታካሂደው ሀገራዊ ምክክር ስኬታማነት ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ገለጸ።

ኮሚቴው በሊጉ የስድስት ወራት የመደበኛ ሥራዎች አፈጻጸም ሪፖርት ላይ በአዳማ ከተማ ውይይት እያደረገ ይገኛል፡፡

የስድስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ፕሬዚዳንት አስፋው ተክሌ ገልጿል፡፡

ወጣት አስፋው አያይዞም ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው  ወጣቶች በህልውና ዘመቻው ወቅት ያሳዩት ተነሳሽነት ለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅርና አክብሮት ያሳዬ ነበር ብሏል።

የሊጉ አመራሮችና አባላት አውደ ውጊያ ድረስ በመሠለፍ፣ ደም በመለገስ፣ ለመከላከያ ገንዘብ በማዋጣትና አስተባብሮ ድጋፍ በማሰባሰብ፣ የዘማች ቤተሰቦችን ሰበል በመሰብሰብ እንዲሁም የአቅመ ደካማ ሰዎችን ቤቶች በመገንባት ርብርብ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግሯል።

ይህ ርብርብ በሌሎች የልማት እንቅስቃሴዎችም ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው ብሏል፡፡

የነጩ ፖስታ ለነጩ ቤተ መንግስት ንቅናቄ ከ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ደብዳቤዎችን ወደ ነጩ ቤተ መንግስት በመላክ የኢትዮጵያን እውነታዎች ለዓለም ለማሳወቅ ንቁ ተሳትፎ መደረጉም በስብሰባው ተነስቷል።

ከጦርነት በኋላ የድል ማግስት መዛነፎችን በጥንቃቄ መምራትና ማስተካከል እንደሚገባም ተመላክቷል፡፡

ወጣቶች ለሀገረ መንግስት ግንባታ፣ ለአካታች ሀገራዊ የምክክር መድረክ ውጤታማነት የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንደሚገባቸውም ተገልጿል።

የብልጽግና ፓርቲ የወጣቶች ሊግ ሥራ አስፈፃሚ ውይይት እስከ ነገ እንደሚቀጥል ተጠቁሟል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም