የኢትዮጵያን ቀደምት አሻራ የሚያሳዩ ስነ ህንፃዎች እድሳት ቅርሶችን ለመጠበቅ የሚያግዝ ነው

99

አዲስ አበባ፣ ጥር 16/2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያን ቀደምት አሻራ የሚያሳዩ ስነ ህንፃዎች እድሳት ከአገልግሎት አሰጣጥ ምቹነት ባለፈ ቅርሶችን ጠብቆ ለማቆየት ጉልህ ፋይዳ እንዳለው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂና ምህንድስና ምሁራን ተናገሩ።


በጥንት ጊዜ በኢትዮጵያ የተገነቡ ህንጻዎች በዘመኑ የነበሩ የግንባታ፣ የማህበራዊ፣ ምጣኔ ሃብትና ባህል እሴቶችን አትመው ይዘዋል።

ከእነዚህ መካከል የሚጠቀሰው የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤትም ታሪካዊ ይዘቱ ተጠብቆና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ታክለውበት እድሳት ተደርጎለት ተመርቋል።

በእድሳቱ ወቅት የህንጻ እድሳት ተቆጣጣሪ መሃንዲሶችን የመሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መምህር ዶክተር ሮባም ሰለሞን፤ የኢትዮጵያን ቀደምት አሻራ የሚያሳዩ ህንፃዎች እድሳት ከአገልግሎት ምቹነት ባለፈ ለቅርስ ጥበቃ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።

የማዘጋጃ ቤት ህንጻ ሲታደስ በህንጻው ውስጥ ያሉ የታሪክ አሻራዎችና የስነ- ህንጻ ጥበቦች እንዳይጠፉ በቅርስ ሙያተኞች ተለይቶ መከናወኑን ገልጸዋል።

እድሳቱ ዓለም የደረሰባቸው ዘመናዊ ግብአቶችን በመጠቀም ለአገልግሎት ምቹ እንዲሆን ተደርጎ መከናወኑን አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በዘመናዊ እድሳት በቤተ መንግስት ግቢ ውስጥ እውን የሆነውን የአንድነት ፓርክ ጨምሮ ሌሎችም ስነ ህንፃዎች ታሪካዊ አሻራቸውን ሳይለቁ መታደሳቸው ይታወሳል።

እስካሁን የተከናወነው የህንፃዎች እድሳት ታሪካዊነታቸውን ጠብቆ ለማቆየት የላቀ ጠቀሜታ እንዳለው ዶክተር ሮባም ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የህንጻ ተቆጣጣሪ መሃንዲስ የሆኑት ኢንጂነር ፋሲል ተበጀ፤ ታሪካዊ ህንጻዎችን ማደስ ምቹና ማራኪ አካባቢ ከመፍጠር በተጨማሪ የተቀላጠፈ አገልገሎት ለመስጠት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

በእድሳቱ የሚጨመሩ አዳዲስ የስነ-ህንጻ ጥበቦች ለሌሎች የግንባታ ፕሮጀክቶች ልምድ መቅሰሚያ እንደሚሆኑም አስረድተዋል።


በኢትዮጵያ የቀደሙ መሪዎች ታሪካዊ አሻራቸውን ያስቀመጡባቸው የስነ-ህንጻና ሌሎች ቅርሶችን ታሪካዊነታቸውን ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ በማስተላለፍ በኩል ክፍተቶች ይስተዋላሉ።

በመሆኑም ታሪክን ጠብቆ ለማቆየትና ከጊዜው ጋር የሚዘምኑ አገልግሎቶችን ለመስጠት ስነ ህንፃዎች ታሪካዊ ይዞታቸው ተጠብቆ እንዲታደሱ ማድረግ ያስፈልጋል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም