የግብርና ዘርፉን ወደ ተሻለ ምእራፍ ለማሻገር እየተመዘገቡ ያሉ ለውጦችን ተቋማዊ በማድረግ መምራት ይገባል -አቶ ሽመልስ አብዲሳ

70


አዳማ ፣ ጥር 16/2014 (ኢዜአ) የግብርና ዘርፉን ለማዘመንና ወደ ተሻለ ምእራፍ ለማሻገር በዘርፉ እየተመዘገቡ ያሉ ለውጦችን ተቋማዊ አድርገን በተቀናጀ መልኩ መምራት ይገባናል ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።


በክልሉ የግብርና ዘርፉን ማዘመን አላማ ያደረገ የሽግግር ምክር ቤት ዛሬ በአዳማ ተመስርቷል።


የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በምክር ቤቱ ምስረታ ላይ እንደገለጹት በክልሉ በግብርና ዘርፍ የታዩ ለውጦችን ተቋማዊ በማድረግ ዘርፉን የማዘመንና ወደ ተሻለ ምእራፍ የማሻገር ስራን እውን ማድረግ ይገባል።


አቶ ሽመልስ አክለውም የቴክኖሎጂ ፈጠራ፣ ማላማድና ማሰራጨት፣ ፈጣን የምርጥ ዘር አቅርቦት፣ የአፈር ማዳበሪያና የአፈር አሲዳማነት የሚቀንሱ የኖራና ተያያዥ ቴክኖሎጂዎችን ማስፋትና ተደራሽ በማድረግ የግብርና ሽግግሩን ስኬታማ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።


የክልሉን የግብርና ዘርፍ ልማት ከተፈጥሮ ዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ ለመስኖ ስንዴ ልማት ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመው አሁን ላይ ከ16 ሺህ በላይ የውሃ መሳቢያ ሞተሮች ተገዝተው ለአርሶ አደሩ መሰራጨታቸውን አመልክተዋል።


ተጨማሪ 4 ሺህ የውሃ መሳቢያ ሞተሮችን ለአርሶ አደሩ ለማሰራጨት ሂደቱ መጀመሩን አንስተዋል።


የተሟላ የመካናይዜሽንና የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ከባህላዊ የአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ እውቀት ጋር በጥናትና ምርምር በማቀናጀት ሽግግሩን እውን ማድረግ የክልሉ መንግስት ቀዳሚ ተግባር መሆኑን አስታውቀዋል።


"የሰብል፣ የቡና፣ ገበያ ተኮር ምርቶችን ጨምሮ አትክልትና ፍራፍሬ ልማትን በአዲስ መልክ ለማካሄድ ምክር ቤቱ ቁልፍ ሚና አለው" ያሉት አቶ ሽመልስ ለተግባራዊነቱ ክልሉን በሰባት ክላስተር በማደራጀት ወደ ልማት መገባቱን አስታውቀዋል።


የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራን ውጤታማ ለማድረግ የተቀረፁ ፕሮግራሞችን ተግባራዊ ለማድረግ የገጠር ፋይናንስ አቅርቦት ስርዓት መዘርጋቱን ጠቅሰዋል።


"ትልቁ ትኩረታችን የግብርና ዘርፉን ወደ ተሻለ ምእራፍ ለማሻገር ተቋማዊ አደረጃጀትና አሰራር በመዘርጋት ምርትን በስፋት፣ በጥራትና በፍጥነት ማምረት ነው" ብለዋል።


በክልሉ ከ35 ሚሊዮን ሄክታር በላይ ለእርሻ የሚውል መሬት መኖሩን የጠቆሙት አቶ ሽመልስ እስካሁን እየታረሰ ያለው 6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር ብቻ መሆኑን ጠቁመዋል።


"የምክር ቤቱ መመስረት የግብርና ዘርፉን ለማሻገር የሚያስችሉ እውቀት፣ መሬትና ውስን ሀብትን አቀናጅተን ውጤታማ ለውጥ ለማምጣት ያስችለናል" ነው ያሉት።


አቶ ሽመልስ ለተግባራዊነቱ የምርምር ተቋማት፣ ዩኒቨርሰቲዎችና በዘርፉ የሚሰሩ ድርጅቶች ሚና የላቀ በመሆኑ ሁሉም የድርሻውን የመወጣት ግዴታ እንዳለበት አስገንዝበዋል።


በተለይ ዋናው የሽግግር ባለቤት የሆነውን አርሶና አርብቶ አደር ተዋናይ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመው የክልሉ መንግስት የተለያዩ ስትራቴጂዎችና ፕሮግራሞች፣ ደንቦችና የአፈፃፀም መመሪያዎችን በማዘጋጀት ወደ ስራ እየገባ መሆኑን አስታውቀዋል።


የመስኖ ስንዴ ልማት፣ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ የአቦካዶ እንዲሁም የማርና ቡና ልማት ላይ አርሶና አርብቶ አደሮች ዋና ተዋናይ በመሆን አመርቂ ውጤት እያስመዘገቡ መሆናቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።


የእንስሳት ሀብት ልማት ዝርያ ማሻሻልና የእንስሳት ስነ ምግብና ጤና ላይ ሰፋፊ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም አመልክተዋል።


"ኦሮሚያ ክልል በሀገር ደረጃ ምሳሌ ሊሆን የሚችል በተለይ በምግብ ራስን ለመቻልና የግብርና ዘርፉን ለማዘመን እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ ነው" ያሉት ደግሞ የግብርና ሚኒስትር አቶ ዑመር ሁሴን ናቸው።


የምክር ቤቱ መመስረት ዘርፉን ለማዘመን ሚናው የጎላ መሆኑን ጠቅሰው ግብርናውን ለማሻገር በክልሉ የሚገኙ የዘርፉ ምሁራን፣ የምርምር ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎች የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።


"ግባችን በምግብ ራስን መቻል ብቻ ሳይሆን ምርትን በስፋት፣ በጥራትና በብዛት በማምረት በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ መሆን መቻል በመሆኑ የተቀረፁ ፕሮግራሞች በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆኑ ሚኒስቴሩ ተገቢውን ዕገዛ ያደርጋል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም