18ኛው የአርብቶ አደሮች ቀን በአርብቶ አደሮች መካከል ይበልጥ መቀራረብን በሚፈጥሩ መርሃ-ግብሮች ነገ ይከበራል - ኢዜአ አማርኛ
18ኛው የአርብቶ አደሮች ቀን በአርብቶ አደሮች መካከል ይበልጥ መቀራረብን በሚፈጥሩ መርሃ-ግብሮች ነገ ይከበራል

አዲስ አበባ፣ ጥር 16/2014(ኢዜአ) የዘንድሮው የአርብቶ አደሮች ቀን በተለያዩ አካባቢዎች በሚኖሩ አርብቶ አደሮች መካከል ይበልጥ መቀራረብን በሚፍጥሩ መርሃ-ግብሮች እንደሚከበር የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
18ኛው የአርብቶ አደር ቀን በዓል "የአርብቶ አደሩ ልማት ለሀገራዊ ብልፅግና" በሚል መሪ ሃሳብ በኦሮሚያ ክልል አዘጋጅነት ነገ ጥር 17 ቀን 2014 በአዳማ ይከበራል።
የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር እና የኦሮሚያ ክልል የመስኖና አርብቶአደር ልማት ቢሮ ቀኑን አስመልክቶ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ሚኒስትሯ ኢንጅነር አይሻ መሀመድ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የአርብቶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻል የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።

የአርብቶ አደር ፖሊሲ ጸድቆ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑንም ለአብነት አንስተዋል፡፡
የዘንድሮው የአርብቶ አደር ቀን በተለያዩ አካባቢዎች በሚኖሩ አርብቶ አደሮች መካከል ይብልጥ መቀራረብን በሚፈጥሩ መርሃ-ግብሮች እንደሚከበርም ነው የተናገሩት፡፡
በእለቱም አርብቶ አደሮች እርስ በርስ እንዲቀራረቡ፤ ምርጥ ተሞክሮዎችን እንዲለዋወጡና ከመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር በመገናኘት በቀጣይ ችግሮቻቸውን በሚቀርፉበት ጉዳይ ላይ እንዲመካከሩ እንደሚደረግም ገልጸዋል፡፡
የአርብቶ አደሮች ቀን መከበር በህዝቦች መካከል መቀራረብን በመፍጠር የህብረ-ብሔራዊ አንድነትን ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚያግዝም ተናግረዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል የመስኖና አርብቶአደር ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሮባ ቱርጫ በበኩላቸው በዓሉን በደመቀ ሁኔታ ለማክበር ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።

በዓሉ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች፣ ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍል የሚመጡ የአርብቶ አደር ተወካዮች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ በአርብቶ አደር አካባቢ የሚገኙ ዩኒቨርስቲ ተወካዮች፣ ባለሃብቶችና ታዋቂ ግለሰቦች በሚገኙበት በድምቀት እንደሚከበርም ተገልጿል፡፡