ብሔራዊ ምክክሩ ልዩነቶችን በመፍታት አገራዊ አንድነትን የማጎልበት ሚና አለው

95

አዲስ አበባ ጥር 16/2014(ኢዜአ) ብሔራዊ ምክክሩ በፖለቲካ ልሂቃን መካከል ያለውን ልዩነት በማጥበብ አገራዊ አንድነትን ለማጎልበት ጉልህ ሚና ይኖረዋል ሲሉ አንጋፋው ፖለቲከኛ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ገለጹ።

በኢትዮጵያ ልሂቃን መካከል መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች በተለይም አገራዊ መግባባት በሚሹ ጭብጦች ዙርያ የሚፈጠረው ተቃርኖ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ በሠላምና መረጋጋት እንዲሁም እድገትና ልማት ላይ እክሎችን ሲፈጥሩ ይስተዋላል።

የዓለም አገራት እንዲህ አይነት ፈተና ሲያጋጥማቸው አገራዊ መግባባት ለማምጣት የተለያዩ ዘዴዎችን የሚጠቀሙ ሲሆን ከእነዚህም አንዱና በብዙ አገራት ተሞክሮ ውጤታማ እየሆነ ያለው አገራዊ ምክክር ነው።

ስኬታማ የዴሞክራሲ ሽግግር ያደረጉ አገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው አካታች አገራዊ ምክክሮችን ማድረግ መሰረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የተሻለ ብሔራዊ መግባባትና መተማመን እንዲኖር ያስችላል።

በተለይም ደግሞ በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ተቀራርቦ የመሥራት ባህልን ለማጎልበት ጠቃሚ መሆኑን ነው የተለያዩ መረጃዎች የሚያሳዩት።

ይህም በመሆኑ ኢትዮጵያም እየተስተዋሉ ያሉ አለመግባባቶችን መፍታት የሚያስችል አገራዊ የምክክር ኮሚሽን አቋቁማለች፤ ኮሚሽኑን የሚመሩት አካላት ዕጩ ጥቆማም ተካሂዷል።

ይህ አገራዊ ምክክር የማያግባቡ ጉዳዮችን እልባት ለመስጠት ትልቅ ሚና እንዳለው ነው አንጋፋው ፖለቲከኛ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የተናገሩት።

እንደዚህ አይነት ምክክሮች ከዚህ ቀደም በአገሪቷ በልሂቃኑ መካከል በሙከራ ደረጃ ለመተግበር እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ የነበሩ ቢሆንም በስፋት ያልተሄደበት እንደነበረም አስታውሰዋል።

ብሔራዊ ምክክሮች ያለፉ ታሪካዊ ጥፋቶችን፣ ስህተቶችና በደሎችንም ጭምር ለመፋቅና ወደ አዲስ ምዕራፍ ለመሸጋገር እንደሚረዳም ገልጸዋል።

በብሔር ብሔረሰቦችና በተለያዩ ማኅበረሰቦች ዘንድ የቆዩ ግጭቶች እልባት እንዲያገኙ በማስቻልም ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት የራሱ ኮሚሽን ተቋቁሞ ሕዝቡንም አካታች አድርጎ የተዋቀረ መሆኑ በልሂቃኑም ሆነ በሕዝቦች መካከል የዘለቁ ታሪካዊ ቁርሾዎችን ለመናድ የሚያስችል ነው ብለዋል።

በምክክሩ ሕዝቡ በስፋት ከተሳተፈና በግልጽነት መወያየት ከቻለ በአገሪቱ ዘላቂ ሠላምና አንድነትን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ትልቅ ተስፋ የሚደረግበት መሆኑንም ጠቁመዋል።   

በአገሪቷ መሰረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚስተዋሉ ልዩነቶችን በመፍታት ወደ አገራዊ መግባባት ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ለውጤታማነቱ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባቸውም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም